በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 100 ቀናት ውስጥ ዶላር በጥቁር ገበያ ለምን ቀነሰ?

የኢትዮጵያ የብር ኖት (በስተግራ) የዶላር ኖት (በስተቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, BBC and Getty Images

ዶላርና ብር ለዘመናት እንደተኳረፉ አሉ። ከሰሞኑ ያሳዩት መቀራረብ ግን ማንም የጠበቀው አልነበረም። ከሳምንት በፊት አንድ ዶላር በ36 ብር ይመነዘር ነበር፤ በጥቁር ገበያ። በዚህ ሳምንት አንድ ዶላር ተመኑ ወደ 31 ብር ወርዷል። በሰባት ቀናት የአምስት ብር ቅናሽ እጅግም ያልተለደመ ነው። ይህ ለምን ሆነ?

የውጭ ምንዛሬ ወትሮም የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ ጤና የሚያሳብቅ የትኩሳት መለኪያ ብልቃጥ 'ቴርሞሜትር' ነው። በተለይም ጥቁር ገበያ ከመንግሥት ቁጥጥር ያፈነገጠ፣ በገበያ ፍላጎት የሚመራ በመሆኑ የተሻለውና የሚታመነው የትኩሳት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ታዲያ የታመመው ምጣኔ ሐብታችን ትኩሳቱ እየበረደለት ይሆን?

ቢቢሲ በዚህ ድንገተኛ የጥቁር ገበያ ዶላር ተመን ማሽቆልቆል ዙርያ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎችን አወያይቷል።

"የድንበር ቁጥጥሩ ይመስለኛል..." ዶክተር ቆስጠንጢኖስ

የዋጋ ከፍና ዝቅ መሬት ላይ ባለ ነገር ብቻ አይከሰትም። በተለይም የምንዛሬ ምጣኔ አንዳች ኮሽታ በተሰማ ቁጥር ሊናጥ የሚችል ድንጉጥ ገበያ ነው። ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ምሳሌን ያነሳሉ።

"የአሜሪካ "ትሬዠሪው" በሚሰበሰብበት ጊዜ ማርኬቱ ገና ስብሰባው ሊካሄድ ነው ሲባል ነው መናወጥ የሚጀምረው"

በተመሳሳይ ከሰሞኑ በድኀረ ዐብይ የተሰሙ፣ የታዩ፣ የተገመቱና የተከሰቱ ዐበይት ክንውኖች የጥቁር ገበያውን ዶላር አደብ ሳያስገዙት አልቀሩም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የውጭ ምንዛሬ ጥሪ ለዳያስፖራው በይፋ ማቅረባቸው፣ በሶማሌ ክልል ነዳጅ የማውጣቱ ዜና፣ በአገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱ ከሚጠቀሱት ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

አፍሪካ በየዓመቱ ከምታገኘው ሁሉን አቀፍ እርዳታ 10 እጥፍ የሚበልጠው በኀቡእ የሚሸሽ ነው። ኢትዮጵያም የዚሁ አካል ናት። ቢሊየን ዶላሮች በሕገ ወጥ መንገድ በየዓመቱ ያፈተልካሉ።

በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አለመረጋጋት ብዙ ዜጎች ገንዘባቸውን በዶላር ቀይረው ወደ ውጭ ያሸሹ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመንግሥት ሹሞች የሚፈጸም ሌብነትና ዝርፍያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ሌቦች' የሚሏቸውን ጨምሮ ጥቁር ገበያውን ሲያንሩት እንደነበር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይገምታሉ።

እነዚህ ዘራፊዎች የአገሬውን ገንዘብ ወደ ባንክ ወስደው ለማስቀመጥ አይችሉም። ጥያቄ ስለሚፈጥርባቸው። ስለዚህ የዘረፉትን ወደ ዶላር በመቀየር ማሸሽን ይመርጣሉ።

አገር በስፋት ስትዘረፍና ብራቸውን ወደ ዶላር መቀየር የሚፈልጉ ዘራፊዎች ቁጥር ሲጨምር የጥቁር ገበያ የምንዛሬ ዋጋ በዚያው መጠን ይመነደጋል።

በብር የሚከፈላቸው የውጭ ተቋራጮች

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ለጥቁር ገበያ ዋጋ መናር ሌላ ምክንያት ይመስለኛል የሚሉት አገር ውስጥ ትልልቅ ግንባታ ለማካሄድ የሚጫረቱ የቻይና ኩባንያዎችን ነው።

እነዚህ ኩባንያዎች ጨረታ የሚገቡት በብር እንዲከፈላቸው በመዋዋል ነው። ነገር ግን በቢሊዮን ብር ከተከፈላቸው በኋላ ብሩን ወደ ዶላር ቀይረው ከአገር ያስወጡታል። ይህን ግብይት የሚያደርጉት ደግሞ በጥቁሩ የዶላር ጉሊት ነው።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደምሳሌ የሚያነሱት ሰሞኑን ድንበር አካባቢ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በትራክ ተጭኖ ሊወጣ ሲል መያዙን ነው። ይህ ዓይነቱ የድንበር ቁጥጥር የጥቁር ገበያ የዶላር ግዢ ፍላጎቱን የቀነሰ ይመስለኛል ይላሉ። ምክንያቱም ኩባንያዎቹ የሕግ ተጠያቂነት ስለሚያስፈራቸው።

የቀድሞው የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ክቡር ገና ግን በዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሃሳብ የሚስማሙት በግማሹ ነው።

"የጠረፍ ቁጥጥር ሲኖር (የዶላር) ገበያውን ቀነስ አያደርገውም አልልም። ተጽእኖ ይኖረዋል። ሆኖም የጠረፍ መዘጋት በዚህ ዓይነት ዶላሩን በአንድ ጊዜ ዝቅ ያደርገዋል ብዬ አላስብም...።"

ከዚያ ይልቅ ይላሉ አቶ ክቡር፣ የአገሪቱ እጣ ፈንታ አሳስቦት፣ ግሽበት አሳስቦት፣ ገንዘቤ ከሚሟሟ ብሎ ብሩን በዶላር የሚያስቀምጠው ሰው ቁጥር በሂደት እየቀነሰ መምጣቱ የዶላሩን የጥቁር ገበያ ተመን እንዲወርድ አንድ ምክንያት ሆኗል።

"ፖለቲካ ላይ ተስፋ ሲታይ የብር ፈላጊ ይጨምራል።"

ለአቶ ክቡር ከሁሉም በላይ ሰሞነኛው ፖለቲካ ለዶላሩ መውረድ ሚና ተጫውቷል። "...የፖለቲካ ችግር እንደሚቀንስ የሚያሳዩ ምልክቶችን አየ፤ የዶላሩ ግዢ ሩጫውን ቀነሰ" ካሉ በኋላ በእንደዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ትርፍ ከፍሎ ዶላር የመግዛት ፍላጎት እየጠፋ እንደሚመጣ ያትታሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው የውጭ ኩባንያዎች አገር ውስጥ የሚያገኙትን ብር በጥቁር ገበያ ስለሚመነዝሩት የዶላር ፍላጎት በጥቁር ገበያ ንሮ እንዲቆይ እንዳደረገው አይጠራጠሩም።

"...በቻይና ኩባንያዎች ለምሳሌ ትልልቅ ሕንጻዎች እየተሠሩ ነው። እነዚህ ኩባንያዎች በብር ነው ጨረታ የሚገቡት። በብር ጨረታ ሲገቡ በብር ነው የሚከፈላቸው፥ በዶላር አይደለም። ስለዚህ የሚከፈላቸውን ብር የማውጫ ዘዴ ይፈልጋሉ። ይህን ፍላጎታቸውን የሚያሟላላቸው ጥቁር ገበያው ነው። በጥቁር ገበያው ብራቸውን ወደ ዶላር ቀይረው በትራክ ወደ ጅቡቲ ወስደው ጅቡቲ ባንክ ተቀምጦ ሕጋዊ ገንዘብ ያደርጉታል።"

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 100 የሥራ ቀናት በቁጥር ሲቀመጡ ምን ይመስላሉ?

"ዶላሩን ይዤ ብቆይ ይሻላል በሚል ፍላጎት አድጎ ነበር" አቶ ክቡር ገና

ወደ ጥቁር ገበያ የሚተመው ደንበኛ መልከ ብዙ ነው። ለስብሰባ፣ ለትምህርት፣ ለሽርሽርና ለሕክምና ወደ ውጭ የሚሄድ ሰዎች ባንኮቻቸው ዶላር ሊያቀርቡላቸው ስለማይችሉ ወደ ጥቁር ገበያ ያቀናሉ።

በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ያገኙ ሹመኞችም ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዳሉ። የግል ባንኮቻቸው እጅ አልፈታ ያላቸው አስመጪ ነጋዴዎች ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዳሉ። ይሄ ሁሉ የጥቁር ገበያው ደንበኛ ነው።

ሌሎች ዜጎች ደግሞ ብራቸውን በዶላር በማኖር የብር ግሽበትን ለመከላከል ይሞክራሉ። ይህ ሁኔታ ዶላር በጥቁር ገበያ ያለውን ዋጋ ከፍ ሳያደርገው አልቀረም።

የጥቁር ገበያው ደንበኛ እንዲህ መብዛት ደግሞ በተዘዋዋሪ የዶላሩን ተፈላጊነት ያንረዋል።

አቶ ክቡር እንደሚሉት ኢ-መደበኛው የዶላር ገበያ በፖሊሲ ሳይሆን በገበያ ፍላጎት የሚመራ ነው። ስለዚህ ፍላጎት ሲጨምር ዋጋው ይጨምራል።

ታዲያ አሁን የዶላር ፍላጎት ቀንሶ ነው ጥቁር የዶላር ተመን የቀነሰው? ሊያውም ፋብሪካዎች በምንዛሬ እጦት በሚዘገቡት ወቅት?

አቶ ክቡር ገናም ይሁኑ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይህንን ጥያቄ በቀጥታ አይመልሱም።

አቶ ክቡር መደበኛው የዶላር ትመና ምጣኔ ሃብቱን የሚመሩት ተቋማት (ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ) በአንድም ሆነ በሌላ ዘዴ የገንዘብ ልውውጡን መጠን፣ ፍጥነትና ሁኔታ እንደሚወስኑ ካብራሩ በኋላ የኢ-መደበኛው የገበያ ባህርያት በአጭሩ ያወሱና አሁን ዶላር በጥቁር ገበያ ለምን ቀነሰ ለሚለው አንኳር ጥያቄ የሚመስላቸውን ያስቀምጣሉ።

አንዱ ወደ ታክስ ሥርዓት ውስጥ ያልገቡ ኩባንያዎች ወደ ጥቁር ገበያ መሄድ ማቆማቸው ነው።

"ወትሮም በመደበኛ ግብይት የቆዩ፣ የታክስ ሥርዓት ውስጥ የቆዩ ኩባንያዎች ወደ ኢ-መደበኛ የዶላር ገበያ አይሄዱም። ወደ ኢ-መደበኛው የሚሄዱት አዳዲሶች ናቸው። በተለያየ ምክንያት።" ካሉ በኋላ "መጪውን ጊዜ በማስላት ዶላር ገበያው ውስጥ ያልነበሩ ሰዎች ገበያ ውስጥ ገቡ። እነሱ የፈሩት ፖለቲካዊ ሁኔታ እየተቀየረ ሲመጣ ከገበያው ወጡ፤ ይህ የጥቁር ገበያውን አረጋጋው " ሲሉ ግምታቸውን ያስረዳሉ፣ አቶ ክቡር።

ከጥቂት ዓመታት በፊት አገሪቱ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች የሚያወሱት ሁለቱም የምጣኔ ሐብት ባለሞያዎች ይህንንም ተከትሎ ነገሮች እስኪጠሩ ድረስ ገንዘቡን በዶላር ማስቀመጥ፣ ወይም ማሸሽ፣ ወይም ዶላሩን ይዤ ብቆይ ይሻላል የሚል ፍላጎት አድጎ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይህ ሁኔታ በአንጻራዊ መልክ እየተለወጠ መምጣቱ ደግሞ የጥቁር ገበያን የዶላር ፍላጎት አረጋግቶታል።

የዐብይ አሕመድ ያለፉት ወራት እንቅስቃሴዎች በዶላር መቀነስ ያለውን ሚና የተጠየቁት አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፣

"በንግግርም ይሁን 'በጀስቸር' ዜጎች ያ የፖለቲካ ፍርሃት ሲቀንስላቸው፣ የፖለቲካው ውጥረት ተንፈስ ሲል የምንዛሬ ሩጫው ይገታል። ይህ ብዙውን ጊዜ ከተስፋ ጋር የሚሄድ ነገር ነው። አገር ሲረጋጋ የብር ፈላጊው እየጨመረ፣ በኢ-መደበኛ መንገድ የዶላር ፍላጎቱ እየረገበ ይሄዳል። ያንን ዶላር በብዙ ትርፍ ገዝቶ የማስቀመጥ ፍላጎቱ እየቀነሰ ሲመጣ ደግሞ የምንዛሬ መጠኑ ወደ መደበኛው ተመን እየተጠጋ ይመጣል።" ይላሉ።

ዶላር በቀጣይ ይቀንሳል ወይስ ይጨምራል?

የውጭ ንግድ ሲፋፋም፣ የአገር ውስጥ ምጣኔ ሐብት ጤና ሲጠበቅ፣ ኢኮኖሚው ለገበያ ክፍት ሲሆን፣ አግባብ ያላቸው የ"ሞኒቴሪ"ና የ"ፊስካል" ፖሊሲ ሲተገበር፣ የፋይናንስ አስተዳደሩ ሲዘምን ጥቁር ገበያ እየቀጨጨ በመጨረሻም አስፈላጊ ወደ ማይሆንበት ደረጃ ይደርሳል።

ይህ ዓለማቀፋዊ የምጣኔ ሐብት ሐተታ ነው። ይህ ሁኔታ ግን እንደየ አገሩ መልክና አስተዳደር ገጽታው ይለያያል።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይህ ችግር የሚፈታው ገበያን በማፍታታት ነው ብለው በጽኑ ያምናሉ። "አሁን ያሉት የአገር ውስጥ ባንኮች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት የሚያስቸል አቅሙም ጉልበቱም የላቸውም።"

ዶላር አሁንም ቢሆን ከእርዳታ፣ ከብድር፣ ከዳያስፖራና ከውጭ ንግድ ምንጮች ነው የሚገኘው። "የውጭ ባንኮች ቢገቡ ግን የራሳቸውን ካፒታል ይዘው ስለሚመጡ የምንዛሬ መንበሽበሽ ሊያመጡ ይቻላቸዋል" ይላሉ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ። ከዚሁ ጋር አብሮ የፋይናንስ አስተዳደሩ እንዲታሰብበት ይፈልጋሉ።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አገሪቱ በሯን እንድትከፋፍት በሚያሳስቡበት መጠን ወጪዎቿን እንድትቀንስ ይወተውታሉ።

ጥቁር ገበያ የሚደራው ከመንግሥት የተዘረፈ ገንዘብ ከአገር ለማሸሽ ሲሞከር ነው። አሁን መንግሥት የራሱን ወጪ እየቀነሰ ሲሄድና ኢኮኖሚውን ክፍት ሲያደርገው ሁኔታዎች እንደሚለወጡ ያስባሉ።

"በፓርቲ የተያዙ ድርጅቶች አሉ፥ በመንግስት የተያዙ አሉ፥ እነዚህ ሁሉ ኢኮኖሚውን ሲያምሱት ምስቅልቅሉ የወጣ የፋይናንስ ሥርዓት ነው የተፈጠረው። መሠረታዊው መልስ የሚሆነው የፋይናንስ ሥርዓቱን ማስተካከል ነው።" ይላሉ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ።

እንደ ስኳር ፋብሪካና ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያባከኑት ገንዘብ እንደማሳያ በማንሳት ጭምር።

አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው አሁን ያለው የጥቁር ገበያ ዋጋ አገሪቱ ውስጥ ተቃውሞ ከመነሳቱ በፊት ከነበረው የምንዛሬ ዋጋ መቀራረቡን ያወሱና በአገሪቱ የተሻለ መረጋጋት እየተፈጠረ ስለመምጣቱ አመላካች እንደሆነ ያትታሉ።

መንግሥት በዳያስፖራ ሃዋላ ላይ ከፍ ያለ ተስፋን ማሳደሩ ግን ብዙም ምቾት አይሰጣቸውም። ከዚያ ይልቅ መንግሥት አገር ውስጥ ምጣኔ ሐብቱን የሚያነቃቃ እርምጃ እንዲወስድ ነው ፍላጎታቸው።

"የጥቁር ገበያው ዶላር ከብር ጋር የሚያሳዩት የምንዛሬ ምጣኔ መጠጋጋቱ እስከየት ይዘልቃል?" ተብሎ የተጠየቁት አቶ ክቡር ፍላጎት እየጨመረ ስለሚሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ 28/29 ድረስ ይወርዳል ብለው እንደማያስቡ ያስረዳሉ።

ከ30 እስከ 32 ድረስ እየዋለለ እንደሚቆይም ግን ይተነብያሉ። ለዚህ ትንበያ ያደረሳቸው ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ምንም አዲስ የተጨመረ ነገር አለመኖሩ ነው።

"እኔ እንደሚገባኝ ከዛሬ ሁለት-ሦስት ዓመት በፊት የነበርነበት ቦታ እየተመለስን እንደሆነ ነው።"