የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ቀጣይ ፈተናዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን ከተረከቡ ሶስት ወራትን አስቆጠሩ። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በውጪ ግንኙነቱና በሌሎችም ዘርፎች የተወሰዱ እርምጃዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው የሚሉ ወገኖች ጠቅላይ ሚንስትሩን እያሞጋገሱ ነው።

የተጨባጭ ለውጥ ሳይሆን ቃል የመግባት ደረጃ ላይ ነን ያሉ በበኩላቸው ከመፍረዳችን በፊት በእውን የሚተገበረውን እንጠብቅ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

አገሪቷን ወደ ሶስት ዓመት ገደማ የናጣት የተቃውሞ ወጀብ ረገብ ማለቱ ከጠቅላዩ መመረጥ ጋር በአንድም በሌላም መንገድ ይገናኛል። ዛሬ ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ሳይሆን የ 'ለውጡን እንደግፋለን' ሰልፍ ይስተዋል ጀምሯል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እርምጃዎች የት ድረስ?

የኢትዮጵያና ኤርትራን የአብሮነት እርምጃ ምን ይፈትነዋል?

ጠቅላይ ሚንስትሩ ተመርጠው ብዙም ሳይቆዩ መገናኛ ብዙሀንን በሰበር ዜና ያጥለቀለቁ ውሳኔዎች ያስተላልፉ ያዙ። ሞት ተፈርዶባቸው የነበሩ ታራሚዎች ነጻ ወጡ። አሸባሪ ተብለው በነበሩ አካለት ምትክ መንግስት "አረ አሸባሪዎቹስ እኛ ነን" አለ።

ከኤርትራ ጋር እርቀ ሰላም የማውረድ ጅማሮ ታየ። ወቅታዊ ዜናዎችን ያደመጡ ኢትዮጵያን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ጋዜጠኞችም "እንዲህ ከሆነማ ወደሀገራችን እንመለሰላን" ብለው ሻንጣቸውን አነሱ።

መንግስት አላስነካም ብሏቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ቴሌ ኮሙኑኬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ መንግስታዊ ተቋማትን ለሀገር ውስጥና ለውጪ ባለሀብቶች ድርሻ እሰጣለሁ አለ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 100 የሥራ ቀናት በቁጥር ሲቀመጡ ምን ይመስላሉ?

በየዘርፉ የተስተዋሉ ተስፋ ሰጪ ውሳኔዎች እንዳሉ ሆነው አገሪቷን ለወደፊት የሚጠብቋት ፈተናዎችስ የትኞቹ ናቸው?

ፖለቲካዊ ውጥረት

በአሜሪካ ጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዮሃንስ ገዳሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የወደፊት ጉዞ ፈተናዎች ሶስት ናቸው።

የመጀመሪያው ፈተና ከገዛ ፓርቲያቸው እንደሚመነጭ ይናገራሉ። የፓርቲው የቀድሞ ልሂቃን የአሁኑ የለውጥ ጅማሮ ላይ ወደ ጎን ተገፍተዋል። የሂደቱ አካል ሆነውም አልታዩም።

መገፋቱ ለልሂቃኑ እረፍት የነሳ እንደሆነ የሚያወሱት ዶ/ር ዮሃንስ ጠቅላይ ሚንስትሩን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጎነትሉ መታየታቸውን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ።

ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች በ100 ቀናት

ሄሎ አስመራ

እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ከሚሉ ብሄር ተኮር ግጭቶችና የሚያስከትሉት የህዝብ መፈናቀል አንፃር የፓርቲው ውስጣዊ ነውጥ እምብዛም ችግር አይሆንም ይላሉ ዶ/ር ዮሃንስ።

በሁለተኛነት የሚጠቅሱት ተግዳሮት የህዝቦች ከቀያቸው መፈናቀል እጅግ አሳሳቢ ከሆነ ሰነባብቷል። የአማራ ክልል ተወላጆች እንዲሁም የኦሮሞ ክልልና የጌዲዮ ማህበረሰቦች መፈናቀል ይጠቀሳል።

"ይህ የሆነው" ይላሉ መምህሩ "ይህ የሆነው ብሄርተኝነት ክፋት ሆኖ አይደለም። ሆኖም አሁን የሚታየው ብሄርተኝነት መጥፎ መሆኑ ነው" ይላሉ። ይህ እሳቸው ከሚከተሉት 'የኢትዮጵያዊነት ይቅደም መርህ' ጋር ይጋጫል ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

አሁን ያለውን ጽንፈኛ ብሄርተኝነት ለመግታት የአስተሳሰብ ለውጥ አብዮት ማምጣት ያሻል። ያ እስኪመጣ ግን ጠንካራ አመራር መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ።

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት ውሰጥ ያለው ሁለት አይነት የአደረጃጀት ስርአት ማለትም ክልሎች ያደጉና ታዳጊ ተብለው መከፋፈላቸው ሌላው ችግር ነው።

ታዳጊ የተባሉት ክልሎች ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያዋስኑ ናቸው። በክልሎቹ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ከመጋጨታቸው ባሻገር ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ሊያሻክሩ ይችላሉ። መምህሩ "ግጭቶቹ ለአገሪቱ ሉአላዊነት ራሱ አደጋ ሆነዋል" የሚሉትም በዚህ ምክንያት ነው።

እንደ መፍትሄ የሚያስቀምጡት የፌደራል መንግስት በክልል ጉዳዮች ጣልቃ ገብቶ ውሳኔ መስጠት ባይችልም ጠንካራ አመራር እንዲሰጥ ነው። በተጨማሪም ማስጠንቀቂያ በማስተላለፍና የፌደራል መንግስቱን አቋም በመገናኛ ብዙሃንን በማስተላለፍ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

ሶስተኛው ጠቅላይ ሚንስትሩ እስከ አሁን ያስመዘገቧቸውን ድሎች እንዴት ያስቀጥላሉ? የሚለው ነው። ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ብንነሳ አገራቱ በቀጣይ በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ይደሳታሉን? የኢትዮጵያንስ ጥቅም እንዴት ማስከበር ይቻላል? የሚሉትን መመልከት ያስፈልጋል።

የህግ ማሻሻያዎችን፣ የሰንደቅ አላማ ጉዳይና ህገ መንግስዊ እስከሆኑት ጉዳዮች ድረስ ዳግም መመልከት ያስፈልጋል። መምህሩ "በእርግጥ ይህ በአንድ ቀን ወይም በአንድ ወር የሚፈታ አይደለም። ሁሉም ደረጃ በደረጃ የሚታይ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በመቶ ቀን ቆይታቸው ያመጡትን ለውጥ ካየን የማስፈፀም ብቃታቸው በጣም ጥሩ ስለሆነ በቀጣይ የሚመጣውን ለመተንበይ ቀላል ነው" ይላሉ።

ያልተመለሱ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች

አገሪቱ ከውስጣዊ የፖለቲካ ውጥረትና የደህንነት ስጋቶች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ መሰናክሎችም ያሉባት መሆኑ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን አስተዳደር ፈተና ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው።

በኪዊን ማሪ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን የምጣኔ ሐብት መምህሩ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) "ፖለቲካዊ መሰናክሎች ችላ ባይባሉም የበለጠ የሚያሰጉኝ የሚጠብቁን የምጣኔ ሀብት ፈተናዎች ናቸው" ይላሉ።

ወደ አሥመራ ለመጓዝ ማወቅ የሚገባዎ 6 ነጥቦች

የ "ጥርስ አልባው" ማዕቀብ መነሳት ፖለቲካ?

ዶላር በጥቁር ገበያ ለምን ቀነሰ?

በኢኮኖሚው የላቀ ድርሻ የተያዘው በጥቂት ሙሰኞች ከመሆኑ በላይ እነዘህ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ በዝባዥ መሆናቸው ያሰጋቸዋል።

ግለሰቦቹ ያላቸውን የአቅም የበላይነት ተገን አድርገው ኢኮኖሚውን ጠልፈው መጣል የሚችሉ መሆናቸው የአዲሱ አስተዳደር ራስ ምታት ይሆናል።

መምህሩ በአሁን ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የዶላር እጥረት በአብነት ይጠቅሳሉ። "ባለፉት አራት ወራት የተባባሰውን የዶላር እጥረት ብንመለከት ለነዚህ ግለሰቦች ዶላርን ከመደበኛው ገበያ ወደ ጥቁር ገበያ ማዘዋወር እጅግ ቀላል ነው" ሲሉ ይገልጻሉ።

ይህም የዋጋ ንረትና የስራ አጥነት መንሰራፋትን ያስከትላል። ህዝቡ በዚህ ሳቢያ ወደ ተቃውሞ ካመራ ሀገሪቱ ዳግም ባለመረጋጋት መናጧ እንዳማይቀር ይገልጻሉ።

መንግስታዊ ተቋማት ወደ ግለሰቦች ይዞታ የሚዘዋወሩበት ውሳኔ መተላለፉም ሌላው ስጋታቸው ነው። ውሳኔው አገሪቱን የባሰ የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደሚዘፍቃት ያስረዳሉ።

እንደ ምክንያት የሚያስቀምጡት መንግስታዊ ተቋማቱን የመግዛት አቅም ያላቸው ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን ነው።

የኋላ ኋላ በማህበረሰቡ መሀከል ያለው የገንዘብ አቅም ልዩነት እየሰፋ ስለሚሄድ ሀገሪቱም ትታመሳለች የሚሉት ዶ/ር ነመራ መንግስት ጠንካራና የማያዳግም እርማጃ እንዲወስድ ያሳስባሉ።

ቀጠናዊ ትስስርና የወደፊት ፈተናዎች

ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከያዙ በኋላ ከአገር ውጪ መጀመሪያ የጎበኙት ጅቡቲን ነበር። አስከትለውም ኤርትራና ኬንያን ጨምሮ ወደ ቀጠናው ሌሎች አገሮችም አቅንተዋል። በጉብኝቶቹ ከአቻዎቻቸው ጋር በዋነኛነት ስለኢኮኖሚያዊ ትስስር ተነጋግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አገሮችን በኢኮኖሚ ከማስተሳሰር ባሻገር የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ ውይይቶቹ ጠቃሚ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህሩ አቶ አዳነ አለማየሁ ይናገራሉ።

የኤርትራን ጉብኝት ብንወስድ የሁለቱ ሀገሮች ለሰላማዊ ግንኙነት ማኮብኮብ ከአገራቱ ባሻገር ለቀጠናውም አለመረጋጋትም እልባት ይሰጣል።

"ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት ተጠያቂ የሚሆኑ ኤርትራ ያስጠለለቻቸው ሀይሎች ለማስከን ይረዳል" ይላል መምህሩ።

የኢትዮጵያ የዕዳ መጠን እየጨመረ ነው

የብር የመግዛት አቅም መቀነስ አንድምታዎች

ላለፉት 20 አመታት ሁለቱ አገራት ሳይታኮሱ ጦርነት ውስጥ ነበሩ። ሰላም ማጣት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያቸው ላይም ተጽእኖ አሳድሯል። የአገራቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር እሰየው ቢያሰኝም በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው ነጥቦችም አሉ።

ሁለቱ አገሮች እርቀ ሰላም አውርደው እንደ ሁለት አገራት እንዲቀጥሉ በመሀከላቸው ያሉ መሰረታዊ መስመሮች መጠበቅ አለባቸው። የሁለቱ ሀገር ዜጎች አንዳቸው በሌላቸው ሀገር ምን መብት ይኖራቸዋል? የሚለውም የህግ ማእቀፍ ያስፈልገዋል።ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር ፍጹም ሰላም ነግሷል ማለት አይደለምና።

በመምህር አዳነ አገላለጽ "ዝም ብሎ ድንበር ከፍቶ 'ኑ ግቡ! ኑ ውጡ!' መባባሉ የተጨማሪ ግጭቶች መነሻ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል።"

ጥያቄን ያዘለው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን

ሁለቱ አገራት በራሳቸው ተነሳሽነት ማለትም ያለ ሶስተኛ ወገን አሸማጋይነት ወደ ስምምንት መምጣታቸው መልካም ነው። ይህን መሰረት በማድረግም ስለ አልጀርስ ስምምነት አፈጻጸም ተወያይተው አንዳች ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።

ሁለቱ አገሮች የጀመሩት የሰላም ጉዞ ምናልባትም አለመተማመናቸውን ይሽር ይሆናል። የጎሪጥ መተያየትን ማስቀረት ግን የነገሩ መጨረሻ አይደለም። ለወደፊት ለሚጠበቁ ውሳኔዎች ግብአት እንጂ። መልካም ግንኙነቱ ካደገ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የምታስከብርበት መንገድ መቀየስ እንዳለባት አቶ አዳነ ያስረዳሉ።

"ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ የምትፈልገው ወደብ ነው" የሚሉት መምህሩ በዋነኛነት የጅቡቲ፣ የኤርትራና የሱዳን ጉብኝት ፍሬያማ እንደሚሆን ያምናሉ።

የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ እንዳይቀር የአጎራባቾቿን ወደብ መጠቀም የግድ ይላታል። ለዚህም ቁልፉ የቀጠናው ሀገራት ራሳቸው እየተጠቀሙ ጎረቤቶቻቸውንም የሚጠቅሙበትን ትስስር እውን ማድረግ ነው።

የቀጠናው አገሮች በኢኮኖሚ ከተሳሰሩ ለጥቅማቸው ሲሉ ወደ ግጭት ከመግባት እንደሚቆጠቡ መምህሩ መላ ምቱን እንዲህ ያስቀምጣሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም... ወዴት? ወዴት?

"የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግርና እንቅስቃሴ የቀጠናው ሀገራትን ወንድማማችነት ያጠናክራል። አገሮቹ ኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ያጠፋል። መንግስታቱም ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል።"

በሌላ በኩል የቀጠናው አገሮች በውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ፣ በተዳከሙ ወይም አቅም ባጡ መንግስታት፣ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትና በአክራሪነት ይፈተናሉ። ቀጠናው የአሜሪካ፣ የቻይና የቱርክና የሌሎች አገሮችም ፍላጎት አለበት። መምህሩ እንደሚለው ቻይና 'በክልሉ ያለኝን ኢንቨስትመንት ለመጠበቅ' ብላ ወታደሮች ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሯ ለህልውናችን አደጋ ነው ይላሉ።

ከቀጠናው አገሮች መሀከል የመንግስታት አቅም ማጣት የመፈራረስ ስጋት የፈጠረባቸው መኖራቸው እሙን ነው። ጠንካራ መንግስት ማጣታቸው የግጭት መንስኤ መሆኑ ከአገራቱ አልፎ ለቀጠናውም አስጊ ነው።

ከቀጠናው አገሮች ምን ያህሉ ዴሞክራሲያዊ ናቸው? ሌላው ጥያቄ ነው። የመንግስታቱ አምባገነንነት እርስ በእርስ የሚፈጸሟቸው ስምምነቶች ፍሬያማ መሆናቸው ላይ ጥያቄ እንደሚያጭር መምህሩ ይናገራሉ።

ሌላው ፈተና አክራሪነት ነው። አልሸባብ በምስራቅ አፍሪካ እስላማዊ መንግስት ማቋቋም ይፈልጋል። ለጥቅማቸው ሲሉ ይህንን ተግባር የሚደግፉ አገራትም ስጋት ናቸው።

የአካባባቢው መንግስታት የሽብር ጥቃቶችን እንዴት ይቋቋማሉ? ከኢትዮጵያ ጀምሮ በተቀሩትም የቀጠናው አገሮች ጽንፍ የወጣ ጎሰኝነትና ብሄርተኛነት አጥልቷል። እነዚህ መሰናክሎች እልባት እስካልሰጣቸው ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያዳግታል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ