"የጌዲዮና ጉጂ ተፈናቃዮች ቸል ተብለዋል" የዓለም ቀይ መስቀል ማኀበር

አይሲአርሲ

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ የደረሰውን ቀውስ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎታል ሲል የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ወቀሰ።

የማኀበሩ የቡድን መሪ ሸሪን ሐናፊ እንደተናገሩት ስምንት መቶ ሺህ ዜጎችን ላፈናቀለው ለዚህ ሰብአዊ ቀውስ የተፋጠነ ምላሽ አለመስጠት የኋላ ኋላ መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም።

በተለይ መጪው የክረምት ጊዜ በመሆኑ በአካባቢው የተለያዩ በሽታዎች ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ማኀበሩ ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን በአካባቢው ጉብኝት ማድረጉን ጠቅሶ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን መረዳቱን አብራርቷል።

ያም ሆኖ በደረሰው ግጭት የተከሰተው ሰብአዊ ቀወስ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ዘንድ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ማኅበሩ ገልጿል።

ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ሰዋዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ እንኳ የሚመች እንዳልሆነ የተናገሩት የማኀበሩ የቡድን መሪ በትምህርት ቤቶች፣ በቢሮዎች፣ በአብያተ-ክርስቲያናት ወለሎች ላይ የሚተኙበትና የሚለብሱት ነገር እንኳን ሳይኖራቸው እያደሩ ነው ብለዋል።

መግለጫው ተፈናቃዮቹ ምግብና ንጹሕ ውሃ እንኳ ማግኘት እንዳልቻሉ ይጠቅሳል።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን በጌዲዮ ዞን ኮቸሬ ወረዳ ለሚገኙና መቶ ሺ ለሚሆኑ ተጎጂዎች በቅርቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል።