ናይጄሪያዊው የአፍሪካው ቁጥር አንድ ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ የሚስት ያለህ እያሉ ነው

Image copyright STEPHANE DE SAKUTIN

ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ የአፍሪካው ቁጥር አንድ ሃብታም አሊኮ ዳንጎቴ ሚስት እየፈለገ ነው ማለቱን ተከትሎ በአፍሪካ የሚገኙ ብዙ የትዊተር ተጠቃሚዎች ለትዳር ዝግጁ ነን እያሉ ነው።

''ወደ ልጅነቴ አልመለስም። ስልሳ ዓመት ቀልድ አይደለም፤ ነገር ግን ዝም ብለህ የሆነችን ሴት ለትዳር አትጠይቅም። ምክንያቱም አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ከሌለበት ምን ያደርጋል።'' ሲሉ አስተያየታቸን ለጋዜጣው ተናግረዋል።

አቶ ዳንጎቴ አክለውም ''በአሁኑ ሰአት በጣም ውጥረት የበዛበት የስራ ዘርፍ ውስጥ ነው ያለሁት ምክንያቱም የነዳጅ ማፈላለግ፤ የማእድን ማውጣት፤ የማዳበሪያ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዝ ላይ ተሰማርተን እየሰራን ነው። ትንሽ መረጋጋትና እረፍት ማግኘት እፈልጋለው'' ብለዋል።

አፎዳ ሳሙኤል የተባለ በናይጄሪያ ታዋቂ ጋዜጠኛ ሰውዬው ሚስት እንደሚፈልጉ ከተሰማ በኋላ ብዙ ሴቶች ምዝገባው የት ነው እያሉ በተደጋጋሚ ደውለውልኛል ሲል በኢንስታግራም ገጹ ላይ አስፍሯል።

አንድ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ ሰውዬው ጾታ የማይመርጥ ከሆነ ለማግባት ዝግጁ ነኝ፤ ምግብ ማብሰል፤ ቤቱን መቆጣጠርና የፈለገውን ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ሲል ብዙዎቹን አስደምሟል።

በትዊተር ተጠቃሚዎች በኩል እየመጣ ያለው የእኔን አግባኝ ጥያቄ ያላስደሰተው ሌላኛው ተጠቃሚ፤ ሰውዬው አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ምን ያህል እንደለፋና ውጤታማ ለመሆን ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ብዙ ቢልም፤ ሰዎች ግን ስለ ትዳር ያወራው ላይ ማተኮራቸው ተገቢ አይደለም ብሏል።

ካለው የስራ ጫና የተነሳም በቀን ለአምስት ሰአት ብቻ እንደሚተኙ የተናገሩት አሊኮ ዳንጎቴ፤ የአርሰናል እግር ኳስ ቡድንን ለመግዛት እቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።