ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአዲስ አበባና ሃዋሳ ጉብኝት ያደርጋሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሥመራ

የፎቶው ባለመብት, FITSUM AREGA/TWITTER

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአሥመራ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከአዲስ አበባ ባሻገር ወደ ሃዋሳ እንደሚያቀኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምኒዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ።

እንዲሁም ሚንስትር መሥሪያ ቤቱን ጠቅሶ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው በአዲስ አበባ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት እንደገና ይከፈታል።

ሚንስትሩ በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም ፊት ለፊት የሚገኘው የቀድሞ የኤርትራ ኤምባሲ እድሳት እንደተደረገለት አስታውቀዋል።

ሚንስትሩ ሕዝቡ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ ጥሪ ባደረጉበትና በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ፕሬዝዳንቱ አትዮጵያ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ የተለያዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ።

ከእነዚህም መካከል እሁድ ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ሰው የሚታደምበት ዝግጅት እንዳለና በዚሁ ስፍራ ሁለቱም መሪዎች ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ጨምሮ ተገልጿል። በዝግጅቱ ላይ ኢትዮጵያዊያንና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ኢሳያስ አፈወርቂ ለጉብኝት ቅዳሜ ሐምሌ 07/2010 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ እራሳቸው ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ማረጋገጣቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ገልፀው ነበር።

የኤርትራ ማስታወቂ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል እንደገለፁት ሳዋ ውስጥ በተደረገ ሥነ-ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከር "በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራ ልዑክ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ይጓዛል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ የሚደርጉት ጉብኝት ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ አመልክተዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በ100 የሥራ ቀናት የት የት ሄዱ? ምን ምን ሠሩ?

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ እንደሚመጡ በተለያዩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ከትናንት ጀምሮ ሲዘገብ የቆየ ቢሆንም ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ በኩል ማረጋገጫ አልተገኘም ነበር፡፡

ይህ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት ከሃያ ዓመታት በላይ ከዘለቀ ጊዜ በኋላ በኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣን የሚደረግ የመጀመሪያው ይፋዊ ጉብኝት ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ወደ አሥመራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከከፍተኛ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት በሁለቱ ሃገራት መካከል ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት የሚያሻሽሉ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለፕሬዝዳንቱ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሚታደሙበት ዝግጅት ላይ የተለያዩ ታዋቂ ድምፃዊያን ዜማቸውን እንደሚያቀርቡም ለመንግሥት ቅርብ የሆኑ ምንጮች እየተናገሩ ነው።

እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም አሊ ቢራ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ሃጫሉ ሁንዴሳ ስማቸው እየተነሳ ካሉት ድምፃዊያን መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።