የኤርትራ ኤምባሲ የማደስ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለፀ

የኤርትራ ኤምባሲ እድሳት በአዲስአበባ

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ተከትሎ፤ ኤርትራ ኤምባሲዋን ዳግም ልትከፍት ነው።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በአዲስአበባ ከተማ ስታዲየም ፊት ለፊት የሚገኘው የቀድሞ ኤርትራ ኤምባሲ እድሳት እየተደረገለት እንደሆነም ገልፀዋል።

የቢቢሲ ዘጋቢዎች በቦታው ተገኝተው እንደታዘቡት መቶ የሚሆኑ ሰራተኞች እድሳቱን ለማጠናቀቅ በመረባረብ ላይ መሆናቸውን ነው።

የግንባታው ሰራተኞች ለቢቢሲ እንደገለፁት እድሳቱን ለማጠናቀቅ 48 ሰዓት እንደተሰጣቸውና ከትናንትና ጀምሮም በመስራት ላይ መሆኑን ነው።

ቦታው የቀድሞ የወጣቶችና ስፖርት ፌዴሬሽን ሆኖ ሲያገለግል የነበረ መሆኑን ገልፀው ጫካውን በመመንጠርም ስራ እንደጀመሩ በተጨማሪ ገልፀዋል።

በመቶ ሺዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነውን የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው የተቋረጠ ሲሆን፤ በየመዲናቸው ያሉትን ኤምባሲዎቻቸውንም ለሁለት ዓስርታት መዝጋታቸው የሚታወስ ነው።