ዛሬ በቂሊንጦ ምን ተፈጠረ?

የመንግሥት መግለጫና የቤተሰብ ጥበቃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለጥየቃ ቂሊንጦ የተገኙ ሰዎች ለቢቢሲ እንደገለፁት ጠዋት ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ ከማረሚያ ቤቱ ሲደርሱ በርካታ ሰው በር ላይ የነበረ ቢሆንም ወደ ውስጥ መግባት ግን አልተጀመረም ነበር።

ከውስጥ ግን ጩኸት ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።

በቅርቡ ከሽብርተኛ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ በፓርላማው እንዲወጣ ከተደረገው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ንቅናቄ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የነበረውና በቅርቡ የተለቀቀው ፍቅረማርያም አስማማው ቦታው ላይ ከተገኙት አንዱ ነበር።

ፍቅረማርያም እንዳለው ከማረሚያ ቤቱ ውጪ የነበሩት ጠያቂ ቤተሰቦች ከውስጥ ምን እንደተፈጠረ ሲጠይቁ 'መፈታት እያለብን አለተፈታንም ስለዚህ አንወጣም ምግብም አንበላም' በማለታቸው ነው የሚል ምላሽ በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተሰጥቷል።

በመጨረሻም ወደ ውስጥ እንዲገቡና ያለውን ሁኔታ እንዲያዩ የተወሰነ ሰው ቢመረጥም እንደገና ማረሚያ ቤቱ አይሆንም ማለቱን ፍቅረማርያም ገልጿል።

"ከዚህ በኋላ ግቢ ውስጥ አስለቃሽ ጭስ ነበር።እሳት አደጋ መኪናዎችም መጡ።አድማ በታኞችም መጥተው ወደ ውስጥ ገቡ።" የሚለው ፍቅረማሪያም እንደገና ቤተሰብ በዋናው በር ሄዶ ጠባቂዎቹ ያለውን ነገር እንዲያሳውቁት ሲጠይቅ በድብደባ መበተን መጀመራቸውን ያስረዳል።

በማረሚያ ቤቱ ውስጥና በእስረኞች ላይ የተፈጠረ ጉዳት ስለመኖሩ ማግኘት የቻልነው መረጃ የለም።