የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል።

ፕሬዝዳንቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ቦሌ ተገኝተው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የተለያዩ ክልል መሪዎችና ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ይህ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በአሥመራ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በምላሹ የሚካሄድ ነው።

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በኤርትራ መሪ ወደ ኢትዮጵያ የተደረገ የመጀመሪያው ጉዞ ነው። ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጉብኝታቸው ለሦስት ቀናት ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚቆዩም የጉብኝታቸው ዝርዝር መረሃ-ግብር ያመለክታል።

በዚህ ጉብኝት ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ በኋላም ለወጣቶች ፌዴሬሽን ተሰጠጥቶ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲ ፕሬዝዳንቱ እንደሚከፍቱት ይጠበቃል። ይህም በሁለቱ ሃገራት መካከል ተቋርጦ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መታደሱን በይፋ ለማመልከት እንደሆነም ተገልጿል።ቦሌ