የኤርትራና የኢትዮጵያ መሪዎች ተገናኝተው ተወያይተዋል፤ ቀጣዩስ ?

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዳቦ ሲቆርሱ

ከጥቂት ወራት በፊት በሁለቱ ሃገራት መካከል በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሰላም ይፈጠራል እንዲሁም መሪዎቹም ተገናኝተው ፊት ለፊት ይነጋገራሉ ብሎ ያሰበ አልነበረም።

መሪዎቹ መገናኝት ዕውን ሆኖ፤ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦችም ዜናውን በደስታ ነው የተቀበሉት፣ ዘፈኑም፣ ጭፈራውም በደስታ ያነቡም አልታጡም።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተደጋጋሚ ዕለቱ ታሪካዊ እንደሆነና እነዚህ ተቃቅረው የነበሩ ህዘቦችን አንድ ላይ እንዴት ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህ ግን የታሪክ ጅማሮ ነው፤ በተለይም ሀገራቱ በጦርነት ከመቋሰላቸው አንፃርና ያልተፈቱ ጉዳዮች በመኖራቸው መጪውን ጊዜ ፈታኝና አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ከመቶ ሺህዎችን በላይ በቀጠፈው፣ የኢኮኖሚ ኪሳራ ባደረሰው የዚህ ጦርነት ጦስ በቀላሉ በሁለቱ መሪዎች ስብሰባ የሚፈታ አይደለም፤ ከዚህም በላይ ስር ነቀል የሆነና ጥልቀት ያለው መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።

የድንበር አተገባበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ ለኤርትራ መንግሥት የሰላም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫም ሊያበቃ እንደሚበቃ ተናግረው ነበር።

በምላሹም የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል"የኢትዮጵያ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የድንበር ውሳኔውን ሲያከብር ነው፤ ይህ እውን የሚሆነው"በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የድንበር ኮሚሽን ከጦርነቱ በኋላ የባድመ ግዛትን ለኤርትራ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የጦርነቱ መቋጫ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የድንበር ኮሚሽኑን ማንኛውንም ውሳኔውን እቀበላለሁ ቢልም ከሁለት ዓመታት በኋላ ባድመ ለኤርትራ መወሰኗን ተከትሎ ተግባራዊ ሳያደርገው ቆይቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ሰራዊት በባድመ ሰፍሮ ቆይቷል።

በቅርቡም ኢህአዴግ የአልጀርስን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለቱ በሁለቱ ኃገራት የነበረውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነበር።

አሁንም አፈፃፀሙ ላይ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎች ያሉ ሲሆን ሁለቱም ሀገራት ጦራቸውን በተጠንቀቅ ለረዥም ጊዜ አቁመዋል።

እነዚህ ወታደሮች የሚነሱበት ወቅት፤ከበላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው አካልና ሂደቱስ ምነ ይመስላል የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያላገኘ ሲሆን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣም ሁለቱ ሃገራት ሊያዩዋቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ በድንበር አካባቢ የሚኖሩትን ማህበረሰብ ዕጣፈንታም አልተመለሰም።

ኢትዮጵያ የአልጀርስን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አደርጋለሁ ማለቷን ተከትሎ የባድመና የኢሮብ ህዝቦች ተቃውሞች አንስተው ነበር፤ ይህም ሁኔታው በቀላሉ ሊፈታ እንደማይችል ጠቋሚ ነው።

ካሳ

የሁለቱ ሃገራት ጦርነት ከመቶ ሺህዎች በላይ ህይወት ቀጥፏል፣ የኢኮኖሚ ውድመትን አስከትሏል።

ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላም የሰላም ሂደቱን ለማፋጠንና የተጎዱትን ለመካስ የካሳ ኮሚሽን በአውሮፓውያኑ 2009 ተቋቁሞ ነበር።

ሃገራቱ የጦርነት ህጎችን ሳያከብሩ፤ የጦር ምርኮኞችንና የሰዎችን መብት በመጣስና ነዋሪዎችን ለአደጋ በማጋለጥ ጥፋተኛ ሆነውም ስለተገኙ ኮሚሽኑ ካሳ እንዲከፍሉ አዟቸዋል።

በውሳኔውም መሰረት የኤርትራ መንግሥት 175 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 161 ሚሊዮን ዶላር ለኤርትራ መንግሥት፣ በተጨማሪ 2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ይገባናል ብለው ለጠየቁ ኤርትራውያን ሊሰጥ እንደሚገባ ወስኗል።

ውሳኔው ዓመታትን ቢያስቆጥርም ሁለቱም ሃገራት እስካሁን ካሳውን አልከፈሉም።

በመሪዎቹም ዘንድ ካሳውን በተመለከተ ውይይት አድርገው ከሆነም የታወቀ ነገር የለም።

ካሳውን በተመለከተም ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃዎች ግልፅ አልሆኑም።