ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ግጭቶችን እንዲያስቆሙ አዘዙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በማርገብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡና ተጠያቂዎቹንም ለፍርድ እንዲያቀርቡ አዘዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት መጠናቀቅን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው።

"በየትኛውም ቀጠና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ የሰው ህይወት የሚያጠፉና የሚያጠፋ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች ከህግ ፊት እንድታቀርቡ። መሀል ገብታችሁ ሃገራዊና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ" ብለዋል።

በተጨማሪም "ሥራችሁን በምትሰሩበት ወቅት ጥፋትና ተጨማሪ ኪሳራ እንዳይኖር ሙያዊ፣ ጥበባዊና በመረጃ የታገዘ ሥራ በመስራት ህዝብ ሳይሞትና ንብረት ሳይወድም ሰላም የሚወርድበትን መንገድ በመፍጠር ብቃታችሁን ማሳየት ይገባል።"

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአላስፈላጊ ግጭቶች ምክንያት የሰው ህይወት እየጠፋ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቅርቡም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የብዙ ሰዎች ህይወት መቀጠፉ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለዚህ ተጠያቂ ያደረጓቸው በቀጥታ የሚሳተፉትን ብቻ ሳይሆን ራቅ ብለው ግጭቱንም የሚያቀጣጥሉትንም አውግዘዋል። በግጭቱና በቀውሱ ግለሰቦችና ቡድኖችም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

"እኛ ዝቅ ብለን ህዝባችንን ከፍ ማድረግ እንጂ ህዝባችን ጫንቃ ላይ ተጭነን ለመንገሥ የምናደርገው ማንኛውም ትናንሽ ሙከራዎች ሄደው ሄደው በታሪክ አስወቃሽ መሆናቸው አይቀርም" ብለዋል።

የመብት ተሟጋቾች፣ አርቲስቶችና ባለሙያዎች "ቆስቃሽና የሚያጋጩ ጉዳዮችን ከማድረግ ይልቅ ሰላምን ላይና የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ" አደራ ብለዋል።

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች ህዝቦችን የሚያጋጩ ሙከራዎች ትርፍ እንደሌላቸው በተጨማሪ ተናግረዋል።

"ሰው ይሞታል፤ ሁሌም ሟች ደሃ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምንናገር ሰዎች ሳንሆን በየሰፈሩ ያለ ደሃ እኛን አምኖና ሰምቶ ህይወቱን ባልተገባ ሁኔታ ስለሚገብር ሰዎች እንዳይሞቱና ንብረት እንዳይወድም፤ ሁላችንም ተባብረን መስራት ይገባናል"ብለዋል።

ሀገሪቷ በአንድነት የምትቆምበት ጊዜ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው "ቀስቅሶ ሰውን ከሰው፣ ቡድንን ከቡድን ማጣላት አዲስ ነገር አይደለም። የኖርንበት የምናቀው ነው፤ የማይበጀንን አምጥታችሁ በስሜት እየተነዳችሁ ህዝብን ከምታባሉ ስሜታችሁን አሸንፋችሁ ህዝብን ብታስታርቁ፤ ህዝብን የሚያገናኝ ድልድይ ብትሰሩ ከታሪክ ተወቃሽነት ትድናላችሁ" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩን መግለጫ ተከትሎ የኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መስተዳደሮች ግጭት በሚከሰትባቸው የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ የፌደራል ፖሊስ አንዲሰፍር መስማማታቸውን ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግለሰቦች እጅ ያለን የውጭ ምንዛሬ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ባንክ ሄደው እንዲመነዝሩ ያሳሰቡ ሲሆን "በርከት ያለ የውጭ ምንዛሬ እያስገባን ስለሆነ፤ ራሳችሁን ከኪሳራ ልትታደጉ ይገባል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥትና የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሬም ሆነ ከፍተኛ ብር ይዘው ለሚመጡ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ያለማንገራገር አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

"ከጥቂት ሳምንት በኋላ የተከማቹ ገንዘቦች ላይ የሚደረጉ ዘመቻዎች ስላሉ፤ ያ ከመፈፀሙ በፊት በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ገንዘባቸውን እንዲያስገቡና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት በማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አደርጋለሁ" ብለዋል።

በተጨማሪም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልፀው፤ ለእንግዳ ተቀባዩ ሕዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። በሁለቱ ሃገራት መካከል ሊናድ የማይችል ግንኙነት እንደተመሰረተ ጠቅሰው ቀጣዩ ሥራ የሁለቱንም ህዝቦች ህይወት ማሻሻል እንደሆነ ተናግረዋል።

ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲም ሥራ መጀመሩ ለወደፊቱ ግንኙነት ትልቅ እመርታ እንደሆነም ተናግረዋል። ሁለቱ ሃገራትም ወደፊት ትልቅ ተስፋ አላቸው ብለዋል።