ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች ምን ያክል አስተማማኝ ናቸው?

የአዲስ አበባ አስመራ መንገድ በከፊል
የምስሉ መግለጫ,

የአዲስ አበባ አስመራ መንገድ በከፊል

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያደርሱ መንገዶችን ደህንነት ይፋ አድርጓል።

እውን መንገዶቹ ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው ለሚለው ጥያቄም የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ አራት ዋና ዋና መስመሮች ለወደፊቱ ለሚደረጉ ጉዞዎች እንደተለዩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አንዳንዶቹ መንገዶች አሁን ባሉበት ሁኔታ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ የተቀሩት ደግሞ ከጥገና እና የአቅም ፍተሻ በኋላ ለአግልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ተነስቶ በጎንደር ወደ ሁመራና በተከዜ ድልድይ አድርጎ ወደ ኤርትራ ግዛት የሚዘልቀው 991 ኪ.ሜ. እርዝማኔ ያለው የአስፓልት መንገድ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፤ ሆኖም የተከዜ ድልድይ ለሃያ ዓመታት ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ ባለማስተናገዱ የደህንነት ምርመራ እንደሚደረግለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ፣ ሞጆ ፣አዋሽ ፣አርባ ፣ዲችኤቶ በቡሬ አድርጎ አሰብ የሚያደርሰው 879 ኪ.ሜ. የአስፓልት መንገድ አብዛኛው ክፍል በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ከደችኤቶ እስከ ቡሬ ጉዞ የሚደረገው በተለዋጭ መንገድ ላይ ስለሆነ በተወሰነ ደረጃ ለአሽከርካሪዎች ፈተና እንደሚሆን አልሸሸጉም።

ከአዲስ አበባ ተነስቶ አዲግራት በዛላምበሳ ወደ አስመራ የሚዘልቀው 933 ኪ.ሜ. አስፓልት መንገድ ለአግልግሎት ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጡት ዳይሬክተሩ፤ ቀሪው ከአዲስ አበባ ፣መቀሌ፣ አድዋ ፣ ራማ ወደ መረብ የሚደርሰው 1005 ኪ.ሜ. የአስፓልት እና ጠጠር መንገድ፤ በተለይ ከአድዋ እስከ መረብ ያለው መንገድ ግንባታ እየተካሄደለት መሆኑን አስታውቀዋል።

የመረብ ወንዝ ላይ ድልድይ በተመሳሳይ የአቅም ፍተሻ ሊደረግለት እንደሚገባም አክለዋል።

መንገዶች በመጠቀም ተሽከርካሪዎች ተጓዦችን መጓጓዝ የሚጀምሩበትን ጊዜ የሚወስነው የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።