ክሳቸው ተቋርጦ በምህረት ከእስር የተለቀቁ ግለሰቦች ለዳግም እስር እየተዳረጉ ነው ተባለ

አቶ በየነ ሩዳ ከአራት ዓመታት በፊት ነበር ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩት።
የምስሉ መግለጫ,

አቶ በየነ ሩዳ ከአራት ዓመታት በፊት ነበር ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩት።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግሥት ክስ በማቋረጥ በምህረት የተለቀቁ ታሳሪዎች ለዳግም እስር እየተዳረጉ መሆናቸውን የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው መምህር አቶ በየነ ሩዳ ባለፈው ሃሙስ ፍቼ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው ለዳግም እስር ከተዳረጉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው ተብሏል።

''በርካታ ፖሊሶች በሁለት መኪና መጥተው ጭንቅላቱ ላይ መሳሪያ ደግነው ይዘውት ሄዱ'' ሲሉ የአቶ በየነ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ እመቤት ሙላቱ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ "አሁን በቁጥጥር የተያዙበት ምክንያት በቅርቡ ከተከሰተ ወንጀል ጋር የተያያዘ አንጂ ከዚህ በፊት ተጠርጥረው በቁጥጥር ከዋሉበት ጋር የሚገናኝ አይደለም" ብለዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩት አቶ በየነ ሩዳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ በክርክር እያሉ ነበር በ2008 ዓ.ም ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት።

የፍርድ ቤት ክርክራቸውን እየተከታተሉ ባሳለፉባቸው ሁለት ዓመታት የጉልበት ስራ እየሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ይደግፉ እንደነበር ባለቤታቸው ወ/ሮ እመቤት ይናገራሉ።

ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በአንድ መዝገብ ስር የነበሩት አቶ በየነ ከአምስት ወራት በፊት መፈታታተቸውን ወ/ሮ እመቤት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''ከእስር ከተፈታ ከቤት ወጥቶ አያውቅም። ልጆቹን አይቶ ሳይጠግብ መልሶ መታሰሩ መላውን ቤተሰብ ከባድ ሃዘን ላይ ጥሏል'' ብለዋል።

በተጨማሪም "መንግሥት የሚለው ሌላ፤ እየተፈጸመ ያለው ሌላ። ህዝብ ይህን ሊያውቅልን ይገባል'' ሲሉ ወ/ሮ እመቤት ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አቶ በየነ የየትኛውም ፓርቲ አባል እንዳልሆኑ ወ/ሮ እመቤት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ከአምቦ ከተማ ለዳግም እስር የተዳረገችው ወጣት ኦብሴ ታዬ ከአምስት ወራት በፊት ነበር ከእስር የተፈታችው።

''ጓደኞቿን ለመጠየቅ ወደ አምቦ ከሄደች ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር መታሰሯን ሰምተናል" በማለት ወንድሟ አቶ አርዓያ ታዬ ይናገራሉ።

አቶ አርዓያ ጨምረው እንደተናገሩት፤ አምቦ ከተማ ላይ በኦሮሚያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ በቢሾፍቱ ከተማ በግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ታስራ ትገኛለች ብለዋል።

ከታሰረች ሁለት ሳምንታት ቢያልፉም እንስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበችና "ጥርጣሬ አለን' ከማለት ውጪ፤ ክሷ ምንድ እንደሆነ አልተነገራትም"አቶ ታየ ብለዋል።

''መንግሥት ወንጀል ፈጽሟል ብሎ የጠረጠረውን ግለሰብ ማሰር አይችልም ማለት ነው?'' በማለት የሚጠይቁት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፤ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል።