ትራምፕ ከፑቲን ጋር በተያያዘ ወቀሳ እየዘነበባቸው ነው

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕና የሩስያ አቻቸው ቭላዽሚር ፑቲን

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩስያው አቻቸው ቭላዲሚር ፑቲን ተገናኝተው መክረዋል። በውይይታቸው ወቅት ትራምፕ የተናገሩት ግን አሜሪካውያን በሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ይበልጥ እንዲሸረሸር እያደረገው ይመስላል።

«ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ የምትገባበት ምንም ምክንያት የላትም» በማለት ከደህንነት መሥሪያ ቤታቸው ተቃራኒ የሆነ ድምፅ ትራምፕ አሰምተዋል።

የአሜሪካ ፓርላማ አፈ ቀላጤ እና ዋነኛው ሪፐብሊካን ፖል ራያን በበኩላቸው «ትራምፕ ሩስያ የአሜሪካ አጋር አለመሆኗ አልገባቸውም መሰል» ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

የዛሬ 10 ዓመት ገደማ ኦባማን በመቀናቀን ምርጫ ያካሄዱት ሌላኛው ታዋቂ ፖለቲከኛ ጆን ማኬይንም «አሳፋሪ ተግባር» ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንት ፑቲን «ከደሙ ንፁህ ነኝ» በማለት ወቀሳውን አጣጥለውታል።

እለተ ሰኞ በፊንላንድ መዲና ሄልሲንኪ የተገናኙት ሁሉቱ መሪዎች ከሁለት ሰዓታት በላይ የወሰደ ዝግ ስብሰባ አካሂደዋል።

ከዚያ በኋላ ባካሄዱት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ትራምፕ መዘዘኛውን ንግግር ያድረጉት።

«ሩስያ የዛሬ 2 ዓመት ገደማ በተደረገው ምርጫ ጣልቃ ገብታለች በማለት የደህንነት መሥሪያ ቤትዎ ይወቅሳል፤ እውን በዚህ ይስማማሉ?» ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ «ኧረ በጭራሽ፤ ምን ሲደረግ ሩስያ በሃገሬ ምርጫ ጣልቃ ትገባለች» በማለት ታሪካዊ ተቀናቃኝ ሃገራቸውን ወግነው ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ አልበቃ ያላቸው ትራምፕ «ባይሆን ከሩስያ ጋር ያለን ጠብ ያለሽ በዳቦ ሊቀረፍ ይገባል» ብለዋል።

የአሜሪካ ደህንነት መሥሪያ ቤቶች ሩስያ በፈረንጆቹ 2016 በተደረገው ምርጫ ጣልቃ በመግባት ሂላሪ ክሊንተን እንዲረቱ ትልቅ ሚና ተጫውታለች በማለት የፑቲንን ሃገር መውቀስ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ትራምፕ ዘግየት ብለው በትዊተር ገፃቸው «በደህንነት መሥሪያ ቤቴ እተማመናለሁ» በማለት ነገሩን ለማቀዛቀዝ ጥረዋል።

ቢሆንም ከትችት መዓት አልተረፉም፤ በዘርፉ አሉ የተባሉ ፖለቲከኞች «አሳፋሪ ድርጊት» እያሉ ሁኔታውን እስኪያብጥለጥሉት ድረስ።

የዴሞክራት ፓርቲ አባል የሆኑ ቻክ ሹመር የተባሉ ግለሰብ «ትራምፕ እኛን እየከፋፈሉ አቅማችንን በማዳከም አጋሮቻችንንም እያስቀየሙ ነው» የሚል መግለጫ አውጥተዋል።

በአሜሪካ አሉ የተባሉ አውራ የደህንነት ሰዎችም ሁኔታው እንዳሳዘናቸው አልሸሸጉም።

የቀድሞው የሲአይኤ ኃላፊ ጆን ብሬናን «የትራምፕ ምላሽ የማይረባ መሆኑ ሳያንስ ሰውየው የፑቲን ኪስ ውስጥ እኮ ነው ያሉት» ሲሉ ነው ሃሳባቸውን ያሰፈሩት።

የትራምፕ ምክትል ማይክ ፔንስ ግን «አለቃዬን አትንኩብኝ» የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።