አሜሪካ ሩሲያዊቷን በሰላይነት ከሰሰች

ማሪያ ቡቲና

የአሜሪካ መንግሥት የ29 ዓመቷን ሩሲያዊቷን የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ ሰርጎ ለመግባት በማሴር ከሷታል።

የተለያዩ የአሜሪካ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ማሪያ ከሪፐብሊካን ፓርቲ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላት ሲሆን የጦር መሳሪያዎችን መያዝ ታበረታታ ነበር ብለዋል።

ይህ ክስ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ሩሲያን ጣልቃ ገብታለች በማለት ስትወነጅል ከነበረው ጋር ተያይዞ ሳይሆን በቀጥታ ከክሬምሊን በተሰጣት ትዕዛዝ ስትሰራ ነበር ተብሏል።

የማሪያ ቡቲና ጠበቃ ሮበርት ድሪስኮል በበኩላቸው ሰኞ በሰጡት መግለጫ "ደንበኛየ ሰላይ አይደለችም፤ የዓለም ዓቀፍ ተማሪ ናት፤ ይህንንም ትምህርቷንም በቢዝነሱ ዓለም ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ዕቅድ ላይ ነበረች"ብለዋል።

ክሱ በጣም የተጋነነ ነው ያሉት ጠበቃው የአሜሪካን ፖሊሲ በየትኛውም ተፅእኖ ውስጥ ለማሳረፍም ሆነ ለማጣጣል ያደረገቸው ሙከራ የለም ብለዋል።

ጠበቃው ጨምረውም ውንጀላውንም ተከትሎ ደንበኛቸው ከተለያዩ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ላይ እየተባበረች መሆኗን ገልፀዋል።

በዋሽንግተን ነዋሪነቷን ያደረገችው ማሪያ ቡቲና እሁድ የተያዘች ሲሆን ረቡዕ ዕለትም ለፍርድ እንደምትቀርብ የፍትህ ዲፓርትመንት በመግለጫው አትቷል።

የመታሰሯ ዜና የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ አቻቸውን ቭላድሚር ፑቲንን ጋር ተገናኝተው ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የአሜሪካ ምርጫ የሩሲያ ጣልቃ ገብነትን ካስተባበሉ ከሰዓታት በኋላ ነው።

"ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ የምትገባበት ምንም ምክንያት የላትም" ብለዋል ትራምፕ።

ከጥቂት ቀናት በፊትም የአሜሪካ የፍትህ ዲፓርትመንት ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የአሜሪካ ምርጫ መረጃን በመጥለፍ 12 ሩሲያዊ የደህንነት ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።