የሐመሯ ወጣት፡ ከሞት አፋፍ ሕልምን ወደ መኖር

ኢሪ ዲማኮ ቾርዲ Image copyright IRI CHORDI
አጭር የምስል መግለጫ ኢሪ ዲማኮ ቾርዲ

ስሜ ኢሪ ዲማኮ ቾርዲ ይባላል። ኢትዮጵያዊትና ፈረንሳዊት ነኝ። አሁን የምኖረው በሞንትሪያል ካናዳ ነው።

ዕድሜዬ አምስት እያለ ነው ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሐመር የወጣሁት። ለነገሩ ስለዕድሜዬ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ምክንያቱም በደቡብ ኢትዮጵያ ዕድሜ አንቆጥርም ነበር።

ቤተሰቦቼ እረኞች ናቸው። እነሱም የአየር ፀባይ ለማወቅ ከዋክብትን በመቁጠር፣ ከብቶቻችውን በማንበብ የሚተዳደሩ ናቸው።

ከሞት መንጋጋ መሹለክ

የተወለድኩበትን ለቅቄ ለመሄድ የተገደድኩት ስለልጆች በነበረ እምነት ምክንያት ነበር። 'ሚንጊ' ይባላል።

በዚያ አካባቢ የአንድ ልጅ ጥርስ ሲበቅል በቅድሚያ የታችኛው ጥርስ ከበቀለ ልጁ ወይም ልጅቱ የተረገመ ነው ወይም ነች ተብሎ ይታመን ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ልጅ በመንደሩ ቢቆይ ለቤተሰቡም ሆነ ለመንደሩ ክፉ ዕጣ ፈንታን ይጠራል ብለው ያስቡ ነበር። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲከሰት ቤተሰቡ ሦስት አማራጮች አሉት።

አንደኛው ጠንቋይ ዘንድ ተሂዶ ኃጢያትን ማንፃት ሲሆን፤ ሁለተኛው እናት ልጇን ከመንደሩ አርቃ ወስዳ ጨክና መጣል ነው። ሦስትኛው አማራጭ ደግሞ የመንደሩ ነዋሪዎች ልጁን በደቦ እንዲገድሉ ማድረግ ነበር።

በዚያን ወቅት አባቴ ሞቶ ነበር። እናቴ ደግሞ አራስ ነበረች። በእቅፏ ሁለት ልጆችን ይዛ ቀርታ ነበር። ልታድነኝ የአቅሟን ሞከረች። ጠንቋይ ዘንድ ወስዳኝ ስትመለስ የሚያምናት ሰው አልነበረም። በመጨረሻም የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ የሚያስኬድ ከተማ ይዛኝ ሄዳ ለሕጻናት ማሳደጊያ ሰጠችኝ። ያም ሆኖ እዚያ ብዙ አልቆየሁም።

አንድ አስተማሪ ከእናቷ ጋር ከሚኖሩበት ቤት ወሰደችኝ። ብዙ ነገሮች ትዝ አይሉኝም። የማስታውሰው ነገር ቢኖር ሁለት የአየርላንድ ሚሽነሪዎች ጋር መኖር እንደጀመርኩኝ ከዕለታት አንድ ቀን ያሳደገችኝ እናቴ ከአጎቴ ጋር መጥተው ሲወስዱኝ ነው።

ከደቡብ ወጥቼ አዲስ አበባ ስደርስ ሁለት ወራት ብቻ ነበር ያለፉት።

ካናዳን በጥበብ ሥራው ያስዋበው ኢትዮጵያዊ

Image copyright IRI CHORDI
አጭር የምስል መግለጫ ኢሪ በተወለደችበት ሃገር ከዓመታት በኋላ

ከአዲሳ'ባ እስከ ካናዳ

17 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ አዲስ አበባ ኖርኩኝ። አባቴ ለሥራ ወደ ኮሎምቢያ ሲላክ ከእናቴ ጋር አብረነው ሄድን። የሁለተኝ ደረጃ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ የቀረኝን የመጨረሻ ዓመት ኮሎምቢያ እንደጨረስኩኝ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ለመጀመር ወደ ካናዳ አመራሁ።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ እስካሁን በካናዳ ነው ያለሁት።

በመሃሉ ወደ አገር ቤት ተመልሼ ነበር።

ከሃገር ከወጣሁ ከአምስት ዓምታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ለሦስት ወራት ያህል ተቀመጥኩኝ። በውስጤ ይመላለሱ የነበሩትን ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘትም ፍላጎት ነበረኝ። ባሳደጉኝም ቤተሰቦቼ እርዳታ ከዘመዶቼ ጋር ወደ ደቡብ አቀናን።

ስሜቶቼ፣ እንባዬ፣ጭንቀቱ፣ምሬቱና ግራ መጋባቱ ከሐሳቦቼ ጋር ተቀላቅለው እንደ መርፌ እዚያም እዚም ይወጋጉኝ ነበር።

ከረሳኋዋቸውም ሆነ ከማስታውሳቸው ሰዎች ጋር መገናኘቱ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር። ተቆጥረው የማያልቁ ዘመዶቼን በማግኘቴና ከእህትና ከአክስቴ ልጆች ጋር ያለኝን መመሳሰል ሳየው በጣም ገረመኝ። አሁን ውስጤ ሰላም ስላገኘ መሄዴን እንደ ስጦታ እቆጥረዋለሁ። ሰላም በመፍጠሬም ሳልሸማቀቅና ሳላፍርበት ስለ ሕይወቴ ማውራት እችላለሁ።

መልካሙ ዜና አሁን በሐመር እንደዚህ ዓይነት እምነት ቀርቷል። እኔ ከመጨረሻዎቹ አንዷ ነበርኩ።

ከእናቴ ጋር ወደ አዲስ አበባ ያመጣኝ አጎቴ እንደነገረኝ ከሆነ መኪና ውስጥ የጂሚ ሄንድሪክስን ካሴት ሲያጫውት አብሬ ለመዝፈን ጊዜ እንዳልፈጀብኝ ያስታውሳል።

ቤት ውስጥ ሁልጊዜም እዘፍን ነበር። አባቴ ደግሞ የድምፅ ትምህርት እንድወስድ ያበረታታኝ ነበር፤ ገና በ11 ዓመቴ።

እራሴን እንዳውቅ ከረዱኝ ትምህርቶች አንዱ ሙዚቃ ነው። በተለይ የአተነፋፈስ ሥልት ሳጠና በጣም ተደንቄ ነበርና ምንጊዜም ቤት ስመለስ ቅልል ያለ ስሜትና ደስታ ይሰማኝ ነበር። ወላጆቼም ፒያኖ እንድማር ገፋፍተውኝ ለስምንት ዓመታት ተምሬያለሁ፤ ብዙም አልገፋሁበትም እንጂ።

ያም ሆኖ መዝፈንና ግጥም መፃፍ እወድ ስለነበር ከሙዚቃ አልተላቀቅኩም።

Image copyright IRI CHORDI
አጭር የምስል መግለጫ ካኢሪ (ግራ)፣ ኢሪ (ቀኝ)

አሁን አብራኝ ከምትዘፍነው ጓደኛዬ ጋር የተዋወቅነው አንድ ሌላ ጓደኛዬ ባዘጋጀችው ምሽት ላይ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እነሆ አብረን እየሠራን እንገኛለን። እሷ ግማሽ ካናዳዊት፣ግማሽ ከቡርኪና ፋሶ ብትሆንም ያጋጣሚ ነገር ስማችን ተመሳሳይ ነው።

እሷ ካኢሪ ትባላለች። ስለዚህ የቡድናችንን ስም ካ-ኢሪ አልነው።በሙዚቃችን የአፍሪካን ሙዚቃ ስልት ከጃዝ፣ ከሂፕሆፕና ከኤሌክትሮኒክ ሙዚቃዎች ጋር እያዳቀልን ነው የምንጫወተው። የመጀመሪያውን ሥራችንን ከሁለት ሳምንታት በፊት በአልበም መልክ ለሕዝብ አቀረብን።

ካለሁበት 5፡'ኑሮዬን ቶሮንቶ ያደረግኩት በአጋጣሚ ነበር'

ካለሁበት 31፡ ''ብዙ ትውስታዎቼ ከዛፍና ከጭቃ አያልፉም''

ሙዚቃ ሕይወቴ

ሥራዬ ብዬ ሙዚቃ መጫወት ከጀመርኩኝ አራት ዓመታት አስቆጠርኩኝ። አምርሬ የያዝኩት ከዛሬ 6 ዓመት ጀምሮ ቢሆንም ግን ከሕጻንነቴ ጀምሮ ለሙዚቃ እንደተፈጠርኩኝ ይሰማኛል።

ሙዚቃ ለመሥራት የሚገፋፋኝ ዋናው ነገር ለነፍሴ የሚሰጠኝ ነጻነት ነው። ስዘፍን በሕይወት እንዳለሁ ይሰማኛል። ሁሉን ነገር ትቶ መላው መንፈሴ በሙዚቃው ውስጥ ይንሳፈፋል።

ብዙውን ጊዜ የምጽፈው ስለ ሰላምና ስለ ይቅር መባባል ነው። በውስጣቸውም መጥፎ ነገሮች ቢያጋጥሙም ሁልጊዜ እንደምንም ብዬ መጨረሻው ወደ ጥሩ ነገር እንዲያዘነብል አደርጋለሁ። በሙዚቃዬ ፍቅርን ማስተማርና ማንፅባረቅ ነው የምመኘው። በሕመም ውስጥ መዳን ይገኛልና።

የተለያዩ የአርት ስልቶችን አቀላቅላለሁ። በማቀላቀሌም ችሎታዬንና ማንነቴን ማንፅባረቅ ችያልሁ። የማህበራዊ ድረ ገፆችን አጠቃቀም እየለመድኩ ቢሆንም በነሱ በኩል ግን ቢያንስ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ እመኛልሁ። ስለተለያዩ ሰዎችና ስለተለያዩ ብሔሮች የሚማሩበት እንዲሆን እፈልጋልሁ። ሰው ስለተፈጥሯዊ ይቅር መባባልና መዳን እንዲማሩ እፈልጋልሁ። ትንሽ ነኝ ብሎ የሚያስበውም ሰው ቢሆን ትልቅ ቦታ እንዳለው እንዲያውቁ ምኞቴ ነው።

Image copyright IRI CHORDI
አጭር የምስል መግለጫ ካኢሪ (ግራ)፣ ኢሪ (ቀኝ)

ሕልምና ምኞቴ

ሕልሜ ሙዚቃዬን ለዓለም ማድረስ ነው። በዚህም ከማምንባቸው ነገሮች አንዱ የሆነውን ፍቅርን መቋደስ ነው። የተለያዩ ቋንቋዎች ተምሬ ደግሞ ዓለምን መዞር እመኛለሁ። ስለተለያዩ ባህሎች ማወቅ፣ ማንነቴን ማወቅ፣ እምነቴንና ደስታዬን ማሳደግም የምኞት ሰንዱቄ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ናቸው።

መቼም ቢሆን ማደግ ማቆም አልፈልግም። ምክንያቱም ይህች ምድር ማቆምያ የላትም። ዓለም ብዙ የምትሰጥን ነገር አለ። እኔም ያለኝን ከመስጠት ወደ ኋላ አልልም። መቼም!

የካናዳ ፓርላማ ዕፀ-ፋርስን ለመዝናኛነት ህጋዊ አደረገ

እኔና ካኢሪ የተለያዩ መድረኮች ላይ ተጫውተናል። ያኤል ናይሚ ለተሰኘ ታዋቂ ዘፋኝ ኮንሰርት መክፈቻ፣ንዊ ዳፍሪክ ላይና ሌሎችም።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ኖማድ በተሰኘው ታዋቂ የሴኔጋል ፌስቲቫል ላይ እንድንጫወት ተጋብዘናልና። ብዙ አጋጣሚዎች እየተከፈቱልን እንድሆነ ይሰማኛል። እኛም ያለንን ፍቅር ለዓለም ለማካፈል ዝግጁ ነን።

በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በቡርኪናፋሶ ቋንቋ (ሳሞ) እንዘፍናለን። ምን ይሄ ብቻ...አንዳንዴም እራሳችን በምንፈጥረው ቋንቋ ጭምር እንዘፍናለን።

ተያያዥ ርዕሶች