ሻምፓኝ እና ፅጌረዳ ያጀበው ከአዲስ አበባ-አሥመራ የመጀመሪያው በረራ

የኢትዮጵያ-ኤርትራ የበረራ መስመሮች
የምስሉ መግለጫ,

የኢትዮጵያ-ኤርትራ የበረራ መስመሮች

ከ400 በላይ ተሳፋሪዎችን ይዞ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ አሥመራ ያቀናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ካሳፈራቸው ከሰዎች እና ጓዝ በተጨማሪ ደስታና ፌሽታን ሳይጭን አልቀረም።

አየር መንገዱ ለተሳፋሪዎች ካቀረበው ሻምፓኝ እና የፅጌረዳ እቅፍ ወዲያ በአውሮፕላን አብራሪው እና በአብዛኛው ተሳፋሪ ፊት ላይ የሚነበበው ስሜት ለዚህ ዋቢ የሚሆን ዓይነት ነው።

«እጅግ ከፍተኛ ደስታ ላይ ነኝ» በማለት ስሜታቸው ያጋሩን ካፒቴን ዮሴፍ ኃይሉ የሚያበሩት አውሮፕላን «የሰላም ጠያራ» በሚል የተሰየመ ነው። አብራሪውም በኤርትራ ምድር የቀድሞ ወዳጆቻቸውን እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል።

«ወደ አደግኩበት ስፍራ ነው ተመልሼ የምበረው። በእውነቱ ተደስቻለሁ» በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምስሉ መግለጫ,

የዛሬው በረራ ላይ መስተንግዶ በከፊል

አውሮፕላኑ በውስጡ ባለስልጣናትን፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ከዓመታት መራራቅ በኋላ ለመገናኘት የተመኙ ተሳፋሪዎችን ይዞ ነበር። የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከተሳፋሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

አቶ ኃይለማሪያም የዚህ ጉዞ ተሳታፊ በመሆናቸው ምን ያህል ደስተኛ መሆናቸውን ባጋሩበት አፍታ በረራውን «ለሁለቱም ሀገራት እና ህዝቦች ወርቃማ ክስተት» ሲሉ አሞካሽተውታል።

ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ የለለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ከሦስት ወራት በፊት የተኩት ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የደረሱበት የሰላም ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የከረመው ቁርሾ ማክተሚያ ሆኗል።

በስምምነቱ መሰረት ዛሬ የተጀመረው የአየር በረራ ገና በዋዜማው የብዙዎችን ቀልብ እና ፍላጎትን ለመሳብ ችሏል። ወደ አሥመራ የሚገዙ ሰዎች ቁጥራቸው ከፍ ያለ ስለነበረ ሁለት ውሮፕላኖች ነበሩ የተጓዙት።

ኤኤፍፒ እነደዘገበውም የመጀመሪያው አውሮፕላን መሬት ከለቀቀ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ዙር ተሳፋሪዎችን የያዘ አውሮፕላን ወደ አሥመራ አቅንቷል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከመቋረጡ በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚያደርሱ 5 የበረራ መስመሮች ነበሩ። የዛሬዎቹ በረራዎች የተጠቀሙት ከአዲስ አበባ-መቀሌ-አሥመራ የሚያደርሰውን መስመር ነው። ቀሪ አራቱ ከሰሞኑ ለሥራ ክፍት እንደሚሆኑና ነባሩ በረራ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።