ጉግል በይነ-መረብን በባሉን ለኬንያ ገጠራማ ሥፍራዎች ሊያቀርብ ነው

ጉግል ኢንተርኔት በላስቲክ ከረጢት ይዞ ኬንያ ገብቷል

የፎቶው ባለመብት, copyrightLOON

ጉግል የተሰኘው ኩባንያ በይነ-መረብን በባሉን ይዞ ወደ ኬንያ ገጠራማ ሥፍራዎች ሊዘልቅ ነው።

የኩባንያው እህት የሆነው ሉን የተሰኘ ተቋም ቴልኮም ከተሰኘው የኬንያ ኔትዎርክ አቅራቢ ድርጅት ጋር በገባው ውል መሠረት ነው ይህን የሚፈፅመው።

ከደመናው በላይ እየተንሳፈፈ የበይነ-መረብ ኔትዎርክ ላላገኛቸው ወደ ኬንያ ገጠራማ አካባቢዎች የሚዘልቀው ባሉን ባላገሩን በበይነ-መረብ ሊያንበሸብሸው እንደሆነ ተሰምቷል።

በዘርፉ ጥርስ የነቀሉ ባለሙያዎች ግን ውሉ ጉግል ኔትዎርኩን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው ሊያደርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ያሻል ይላሉ።

በሰማይ በራሪው ከረጢት የኬንያ መንግሥት በራሱ አቅም ኔትዎርክ ሊያደርስ ወዳልቻለባቸው ሥፍራዎች ነው የሚዘልቀው።

ድርጅቱ ሥራውን በቅርቡ እንደሚጀምር እንጂ ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ለጊዜው ይፋ አልሆኑም።

«ሉን ከተባለው ድርጅት ጋር ሆነን ይህን ለየት ያለ ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ለማንሳፈፍ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም» ሲሉ የቴልኮም ሥራ አስኪያጅ አልዶ ማሬውስ ተደምጠዋል።

ከባህር ወለል በላይ 20 ኪሎ ሜትር አካባቢ ከፍ ብሎ እንደሚንሳፈፍ የተነገረለት ከረጢት ከአየር ትራፊክ ጋር ተስማምቶ ነው የሚንቀሳቀሰው።

ከመብረቅ አደጋ እንዲጠበቅ ተደርጎም ነው የተሠራው ያሉት ፈጣሪዎቹ ከሰማይ በራሪ እንስሳትም ጋር ያለው ቁርኝት የወዳጅነት ነው ሲሉ አስረግጠዋል።

ባለአንቴናው ከረጢቱ የአንድ ሜዳ ቴኒስ መጫወቻን ያክል ግዝፈት እንዳለው ተጠቁሟል።

ዜናውን የሰሙ 'አጀብ! ከደመናው በላይ ያለኸው ከረጢት እስቲ የአንድ ቀን ጥቅል አገልግሎት ጠብ አድርግልን የምንልበት ጊዜ መጣ?' እያሉ ነው እየተባለ ነው።