አብረሃም መብራቱ፡ «ቡድኑን ስኬታማ የማድረግ ሕልም አለኝ»

አብረሃም መብራቱ፡ 125 ሺህ ብር ተከፋዩ ኢትዮጵያዊ Image copyright YASSER AL-ZAYYAT

አብረሃም መብራቱ አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ለመሥራት ተስማማቷል። አሰልጣኝ አብረሃም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለስ አሳውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ሳምንት አምስት ዕጩ አሰልጣኞችን አወዳድሮ አብርሃም መብራቱን አሰልጣኝ ለማድረግ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

በዚህም መሠረት የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው ለማገልገል መስማማታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት አብረሃም መብራቱ፤ በጦርነት የተመሳቀለችው የመንን ለእስያ ዋንጫ ማብቃት ችለዋል።

«በሌሎች ዝርዘር ጉዳዮች ላይ ሃገር ቤት ገብቼ ከተነጋገርን በኋላ ውል የምፈርም መሆኔን አሳውቄያለሁ» ብለዋል።

• አብረሃም መብራቱ፡ የየመንን ብሔራዊ ቡድን ለትልቅ ውድድር ያበቃ ኢትዮጵያዊ

''ብሔርተኝነት'' እያጠላበት ያለው እግር ኳስ

አሰልጣኝ አብረሃም ውል ከሚገቡበት ጊዜ አንስቶ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ኮንትራት እንደሚፈራረሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

«ለሁለት ዓመት የሚቆይ ውል የሆነበት ምክንያት ጊዜ ወስጄ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መመሥረት የሚያስችለኝ ጊዜ አገኝ ዘንድ ነው» ይላሉ አሰልጣኙ።

ምክትል አሰልጣኝ የመምረጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች የአሰልጣኙ ኃላፊነት እንደሆኑም አቶ አብረሃም አስረድተዋል።

ደሞዝዎት 125 ሺህ የተጣራ የኢትዯጵያ ብር ነው የሚባለው ምን ያህል እውነት በሚሰል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ «ፌዴሬሽኑ የተጠቀሰውን መጠን ሊከፍለኝ ዝግጁ ነው፤ በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ዙሪያም ስመጣ የምንወያይ ይሆናል። ነገር ግን የገንዘቡ ጉዳይ ብዙም የሚያሳስብ አይደለም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

Image copyright Alkass

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እረፍት ላይ በሚገኝበት ሰዓት የአሰልጣኝት መንበሩን የሚረከቡት አቶ አብረሃም «ለብሔራዊ ቡድን የሚመጥን ቡድን በአጭር ጊዜ ማቋቋም አንዱ ፈተናዬ ሊሆን ይችላል፤ ግን ይህን ለመቅረፍ ሃገር ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር እሠራለሁ» ይላሉ።

«የወቅቱ የብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቡ አቶ ሰውነት ቢሻው ናቸው፤ ከእርሳቸው ጋር በመሥራት የመጀመሪያው ፈተናዬን እንደምወጣ አስባለሁ።»

«ከወቅቱ የፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና የሥራ አጋሮቻቸው ጋር ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መሥራት የሚያስችሉኝን አማራጮች የምወያየው ሃገር ቤት ስመለስ ነው» ሲሉ ያክላሉ አሰልጣኙ።

ቢጫና ቀይ ካርዶች እንዴት ወደ እግር ኳስ ሜዳ መጡ?

የእግር ኳስ ማልያዎች ለምን ውድ ሆኑ?

የ48 ዓመቱ አሰልጣኝ አብረሃም «ማንኛውም የስፖርት ቤተሰብ እንደሚጠብቀው ስኬታማ የሆነ ቡድን የመስራት ሕልም አለኝ» በማለት የወደፊት ዕቅዳቸውን አስቀምጠዋል።

አሰልጣኝ አብረሃም በፈረንጆቹ 2019 ወርሃ ጥር ላይ ለሚከናወነው የእስያ ዋንጫ ያሳለፉትን የየመን በሔራዊ ቡድን የለቀቁት ቡድኑ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ነው።

አሰልጣኝ አብረሃም ከየመኑ ሥራቸው በተጨማሪ የቡና፣ የኒያላ፣ የወንጂ ስኳር እና የእህል ንግድ አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ላለፉት ሰባት ወራት ያለ አሰልጣኝ መቆየቱ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ