በምሥራቅ ወለጋ የአራት ቀን ሬሳ አስነሳለሁ ብሎ መቃብር ያስቆፈረው 'ነብይ' በቁጥጥር ሥር ዋለ

እራሱን ነብይ የሚለው ግለሰብ ሟችን ለማስነሳት ሲጥር Image copyright Screen Capture/Facebook
አጭር የምስል መግለጫ እራሱን ነብይ የሚለው ግለሰብ ሟችን ለማስነሳት ሲጥር

አቶ በላይ ቢፍቱ የሊሙ ወረዳ ገሊላ ከተማ ነዋሪ ነበሩ። ባሳለፈነው ሰኞ ነበር በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው።

ቤተሰብ ሃዘን ተቀምጦ ሳለ ጌታያውቃል አየለ የሚባል ግለሰብ ለሟች ቤተሰቦች የመጽሐፍ ቅዱሱን አልአዛር ታሪክ ከነገራቸው በኋላ ሟቹ በላይን እንደሚያስነሳ ይነግራቸዋል።

ከዚያም በላይን ከሞት እንደሚያስነሳ የቤተሰብ አባላቱን ካሳመነ በኋላ በላይ ወደተቀበረበት ወደ ሙሉ ወንጌል የመቃብር ስፍራ ይዟቸው ሄደ።

ሰባኪው አውሮፕላን ግዙልኝ አለ

በደቡብ ኢትዮጵያ አጥማቂው በአዞ ተገደሉ

በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ የነበሩት የሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዲንሳ ደበላ ''ከመቃብሩ ስፍራ በላይ ከሞት ይነሳል የሚል ተደጋጋሚ ድምጽ ሰምቼ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማጣራት ወደ ስፍራው ሄድኩ'' ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ድርጊቱ የቤተክርስቲያኒቷን ስርዓት እንደሚጻረር በመንገር ድርጊቱ እንዲቆም ሲያሳስቡ ከግለሰቦቹ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ሲል ሸሽተዋል።

ከዚያም ጌታያውቃል የተባለው ግለሰብ መቃብሩን አስቆፍሮ የሬሳ ሳጥኑን ከከፈተ በኋላ በተደጋጋሚ ''በላይ ተነስ'' እያለ ሲጮህ ነበር።

በዚህ ብቻ ያልተቆጠበው ይህ ግለሰብ የሬሳ ሳጥኑ ላይ ተዘርግቶ በመተኛት 'ተነስ' እያለ በተደጋጋሚ ድምጹን አሰማ።

ራሱን ነብይ እያለ የሚጠራው ይህ ግለሰብ ከላይ የተጠቀሰን ድርጊት ሲፈጽም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ በርካቶች ሲቀባበሉት ውለዋል።

በመጨረሻም መልስ ያጣው ግለሰብ ''ምንም ማድረግ አይቻልም'' ብሎ ከመቃብሩ ጉድጓድ ውስጥ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጉዳይን በአትኩሮት ሲከታተሉ የነበሩ የአካባቢው ሰዎች እና የቤተሰብ አባላት በግለሰቡ ድርጊት በመበሳጨታቸው ሊደበድቡት ተነሱ ሲሉ አቶ ዲንሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዘግይቶ በአካባቢው የተገኘው ፖሊስ አቶ ጌታያውቃልን ከመደብደብ አትርፎት በቁጥጥር ስር አውሎታል። ''አሁን በቁጥጥር ስር ይገኛል'' ሲሉ የሊሙ ወረዳ የፖሊስ አባል የሆኑት ኮማንደር ታደሰ አማኑ ነግረውናል።

''ግለሰቡ የፈጸመውን ድርጊት እያጣራን ነው። ነብይ ነኝ የሚለው ይህ ሰው በአካባቢው ያሉ የየትኛውም ቤተክርስቲያን አባል እንዳልሆነ አረጋግጠናል'' ሲሉ ለቢቢሲ ጨምረው ገልፀዋል።

ይህ ግለሰብ የወረዳው ጤና ቢሮ ባልደረባ ስለመሆኑም ከምንጮቻችን መረዳት ችለናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ