በባሌ ዞን ጎባ ከተማ በተፈጠረው ግጭት የስድስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተገለፀ

በጎባ ከተማ ባጋጠመ ግጭት ስድስት ሰዎች ሞቱ Image copyright Getty Images

በባሌ ዞን በጎባ ከተማ ባለፉት ቀናት በተፈጠረ ግጭት የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የከተማዋ ከንቲባ ዘይነባ ጣሀ ተናግረዋል። በርከት ያሉ ሰዎች ደግሞ በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነውም ብለዋል።

ግጭቱ የተጀመረው በባሌ የኦሮሞ ገበሬዎች ትግል ወቅት ግንባር ቀደም ታጋይ የነበሩት የሀጂ አደም ሳዶን ሐውልት በከተማዋ በሚገኝ አደባባይ መገንባትን በመቃወም ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ሐውልት የመገንባት ጥያቄው በአካባቢው ነዋሪዎች እና ሽማግሌዎች የቀረበ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህንን ጥያቄም መንግሥት ተቀብሎት ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ከንቲባዋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጎባ ተወላጆች ከኦሮሚያ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ

''የኤርትራ ኢኮኖሚያዊ ዕቅድ የተነደፈው በኢትዮጵያ ሃብት ላይ ነበር'' አምባሳደር አውዓሎም ወልዱ

ሐውልቱ ሊቆም በታሰበበት አደባባይ ላይ ቀድሞ የነበረ የቀይ ቀበሮ ሐውልት አይፈርስም፤ የታሰበው ሐውልትም ሌላ ቦታ ላይ ይተከል የሚሉ ነዋሪዎች ቅሬታ ያቀረቡ መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባዋ ይህ ቅሬታም ዞን ድረስ መድረሱን ተናግረዋል።

በከተማዋ ነዋሪ የሆነና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ ለቢቢሲ ሲያስረዳ በተፈጠረው ሁኔታ ላይ ከከንቲባዋ ሀሳብ ጋር ይስማማል። "የቀይ ቀበሮው ሐውልት ቀይ ቀበሮ እንኳን አይመስልም" ሲል የተቃውሞው ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ መሄዱን ያስረዳል። እንደ እርሱ እምነት በዚህ ግጭት ሌሎች ኃይሎች እጃቸው አለበት ይላል።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የባሌ ዞን አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር መወያየታቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት አካላት አብዛኛዎቹ የሐውልቱን መተከል ይቃወሙት እንደነበር ያስታውሳሉ።

የሚቃወሙበትም ምክንያትም ከሐይማኖት ጋር እንደማይገናኝ አስረድተው ሀውልቱ መቆም እንደሌለበት በደፈናው ተቃውመዋል ብለዋል ከንቲባዋ።

ከንቲባ ዘይነባ ጣሀ ሐሙስ ዕለት በከተማዋ የግጭት ምልክቶች መታየታቸውን ሰዎች በየፊናቸው በመሆን ይዝቱ አንደነበር ያስታውሳሉ።

የቻይና ግዙፍ ማሽኖች

ማንዴላን ውትድርና ያሰለጠኑት ኢትዮጵያዊ

አርብ ዕለት በርከት ያሉ ከገጠር ቀበሌዎች ዱላ ይዘው የመጡ ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ እንደገቡ፤ እንዲሁም አስተዳደሩ የመጣችሁት ለሰላም ከሆነ ዱላችሁን ጣሉ በማለት በርካቶች ዱላቸውን መጣላቸውን የተወሰኑም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

"እነዚህ ወደ ከተማዋ የገቡ ሰዎች ቅዳሜ ዕለት መንግሥት ሳያውቅ ማለዳ ወጥተው የቀይ ቀበሮውን ሐውልት አፈራረሱት። ይህ ሲሆን ምንም አይነት ግጭት አልተፈጠረም። ሐውልቱን አፈራርሰው ከከተማዋ እየወጡ እያለ በአቅራቢያው ከሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደወል ድምፅ ተሰማ" የሚሉት ከንቲባዋ ይህንን የደወል ድምፅ የሰሙ የከተማዋ ነዋሪዎች መሳሪያ ታጥቀው ወጡ በማለት ግጭቱ መልኩን መቀየሩን ያስረዳሉ።

ከዚህ በኋላም ከተማዋን ለቅቀው እየወጡ ከነበሩ ሰዎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ የሰው ህይወት ላይ አደጋ ደርሷል ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ተናግረዋል።

ከተማዋ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ነበሩ የሚሉት ከንቲባዋ የኦሮሚያ ፖሊስ ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ እስከ 12 ሰዓት ድረስ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ሲታኮሰ መዋሉን ሁኔታውን ለመቆጣጠር ግን ከአቅም በላይ እንደሆነበት ይናገራሉ።

በዕለቱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች አብዛኞቹ በጥይት ተመትተው እንደሆነ ለቢቢሲ ያስረዱት ከንቲባዋ አሁን መረጋጋት እንደታየም ጨምረው ተናግረዋል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የጎባ ከተማ ነዋሪ ወደ ከተማዋ በርካታ መሳሪያ ገብቷል የሚል ወሬ በሰፊው ይናፈስ እንደነበር ያስታውሳል። ነገር ግን እርሱ በዓይኑ ያየው ምንም አይነት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ገልጿል።

ከንቲባ ዘይነባ የከተማው አስተዳደር በነገው ዕለት ነዋሪዎችን ለማነጋገር እቅድ እንደያዘ ገልፀዋል።

ሐጂ አደም ሳዶ በባሌ የኦሮሞ ገበሬዎች ትግል ወቅት ግንባር ቀደም የነበሩ ግለሰብ ሲሆኑ በኋላ ላይም በእነ ጄነራል ታደሰ ብሩ የሚመራው ሜጫና ቱለማ ማህበር የቦርድ አባል ነበሩ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ