"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበራቸው ውይይት

"ኢህአዴግ 27 ዓመት ከነበረበት ጫና ወጥቶ እየተጠናከረ ነው ያለው እንዳትዘናጉ። አሁን ባደረግነውና ወደፊት በምናደርገው መሻሻል ስለምንቀጥል፤ ህዝብ ወደእኛ እየመጣ ነውና እንዲህ ተበታትናችሁ እኛን መደራደር አትችሉም። ህብረት ፈጥራችሁ በመደራጀት ጥሩ ተፎካካሪ ሆናችሁ ውጡ" የሚል መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከአምሳ በላይ ሃገር አቀፍ፣ ክልላዊና ከውጭ ሀገራት ከመጡ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።

ውይይቱ ምን ላይ ያተኮረ ነበር?

ለዓመታት በጠላትነት ሲተያዩ የነበሩት የተለያዩ ፓርቲዎች አንድ ላይ በመጡበት በዚህ መድረክ ላይ በቅርቡ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች፣ መደረግ ስለሚገባቸውና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርስ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ውይይት እንደተደረገ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ገልፀዋል።

አቶ አበበ እንደሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ መሻሻል ስለሚገባቸው ተቋማት የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማት ፣ የመከላከያና ደህንነት፣ እንባ ጠባቂና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለልተኛ ሊሆኑ እንደሚገባቸውም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በተለይም ከምርጫ ህጉና ከምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ቢያነሱዋቸውም የኢህአዴግ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንደነበር የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ ገብረ-ማርያም ይናገራሉ።

በ1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ የተወሰነ መሻሻል ቢደረግም አሁንም በህጉ ላይ ያሉ ክፍተቶችና የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆን ማነቆ እንደሆነ ይገልፃሉ። በቅርብ ጊዜም ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ድርድር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ከሁለት ወራት በኋላ ድርድሩን አቋርጠው መውጣታቸውን አቶ አበበ ተናግረዋል።

"የምርጫ ቦርድ ላይ የኢህአዴግ እጅ ረዥም ነው። ከተመልካቾችና ከታዛቢዎች ምልመላ ጀምሮ በርካታ ክፍተቶች አሉበት። በምርጫ ለመወዳደር ያለው የፖለቲካ ጫና ከፍተኛ ነው" የሚሉት አቶ አበበ ይህም እንደሚቀየር ተስፋቸውን አስቀምጠዋል።

ምንም እንኳን የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 39 እና 40 ለአስርት ዓመታት አወዛጋቢ ቢሆኑም ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የህገ-መንግሥቱ አለመከበር ዋናው ችግር መሆኑንም አቶ ገብሩ ይናገራሉ።

"ሕገ-መንግሥቱ ከነችግሩም ቢሆን እያከበርነው ነው። ዋናው ችግር ግን ኢህአዴግ ራሱ ያወጣውን ሕግ ተግባራዊ አለማድረጉ ነው። ሕገ-መንግሥቱ መተግበር አለበት" ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በአጭር ጊዜ ሊፈቱ ይገባል ያሉዋቸውንም ጉዳዮች ያቀረቡ ሲሆን በሀገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶች እንዲፈቱና በተለይም አሳሳቢ የሆነው የህዝብ መፈናቀል፤ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል፣ በጉጂ ዞን መቆም እንዳለበትና መልሶ ማቋቋም ላይ ሊሰሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ተነጋግረዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ ገብረ-ማርያም በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተደረጉ ስላሉ ማሻሻያዎች አመስግነው በተቋም ደረጃ የሚመሩና የሚመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል። "ማሻሻያዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቃደኝነት ጥገኛ መሆን የለባቸውም፤ በተቋም የሚመሩ መሆን አለባቸው" ይላሉ።

"እኛም እንደመር ስንል የኖርነው ኢህአዴግ አልደምራችሁም ብሎን ነው ይህቺ ሃገር መከራ ላይ የወደቀችው፤ ይህም እየተሻሻለ ነው ግን በተቋማት መደገፍ አለበት" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ

"ኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ከመመስረት ውጭ አማራጭ የላትም፤ ይህም የሰብዓዊ መብትን፣ ህግን በሚያከብሩ ተቋማት መደገፍ አለበት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው የሚወጡበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፓርቲዎች ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ ግንባር በመመስረትና በመቀናጀት መስራት አለባቸው የሚል መልእክት እንዳስተላለፉም አቶ አበበ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

"በተናጠል የሚደረገው ትግል የትም አያዘልቅም። ወደፊት ዲሞክራሲያዊ የሆነች ሀገር ለሁላችንም ስለምታስፈልገን በምርጫ ፖለቲካ ብቻ የመንግሥት ስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ለማስቻል የፓርቲዎች ጥንካሬ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተነጣጥለው የሚያደርጉት ትግል አዋጭ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ቢሆንም ለመደራጀትና ግንባር ለመፍጠር ተቃዋሚዎች አዲስ እንዳልሆኑ አቶ ገብሩ ይናገራሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ ሃገር ተቃዋሚዎች ተሰባስበው የመደራጀት ጉዳይ በውል ይወቁት አይወቁት አላውቅም እንጂ፤ ለዓመታት ተደራጅተን ሰርተናል" የሚሉት አቶ ገብሩ፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ፕሮግራም የሌላቸው፣ የአባል ቁጥራቸው ከአስር የማይበልጥና፣ ፖሊሲ ያልቀረፁ ተቃዋሚዎች በስም እንጂ የፓርቲን መስፈርት እንደማያሟሉ ይናገራሉ።

"ምርጫ ቦርድ ቢኖር ይህንን ያጠራዋል" ይላሉ።

ከአቶ ገብሩና አየለ በተጨማሪ አቶ ሌንጮ ለታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥጋቢ መልስ እንደሰጡ ይናገራሉ።

"ተቋማት ዲሞክራሲያዊ ለሆነ ባህል አመቺ ሆነው እንዲዋቀሩ፤ ከዚህ በፊት ከፓርቲ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበራቸው ተቋማት ነፃ እንዲሆኑ ውይይቶች ነበሩ" ይላሉ።

ከዚህ በተቃራኒ ውይይቶቹ መልካም እንደበሩ ቢጠቅሱም የአረናው አቶ ጎይቶም ፀጋዬ አቅርበዋቸው የነበሯቸው ጥያቄዎች እንዳልተመለሱ ይናገራል።

የኢትዮ-ኤርትራ እርቅን በተመለከተ በተለይም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ስላላቸው ስጋት ማብራሪያ ቢጠይቁም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነቱን የሚወስዱ ግለሰቦች በአጭር ጊዜ እናሳውቃለን የሚል ምላሽ ቢሰጡም እስካሁን ምላሽ አለመሰጠቱን ቢጠቅሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንዳላሉ አቶ ጎይቶም ይናገራሉ።

ሊደረጉ ስለሚገባቸው ማሻሻያዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎቹን የምርምር ወረቀት እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል በዚህም መሰረት አቶ ሌንጮ ለታ ስለማሻሻያዎች፣ ለሀገሪቷ ምን አይነት ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል ለሚለው ኢዴፓና ሰማያዊ ፓርቲ፣ ብሔራዊ መግባባትና ሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ለአረና ፓርቲ፣ ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ ላይ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል የሚባሉ ጉዳዮችና ውይይቶች ላይ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው የተሰጣቸው ኃላፊነት "የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል አብዮት ወይስ ማሻሻያ" የሚል እንደሆነ ገልፀው፤ "እስከዛሬ የተደረገው አብዮት እንጂ ማሻሻያ አልተደረገም" ይላሉ።

ከሁለት ወራት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ የያዙ ሲሆን ኢህአዴግ ስር ነቀል ማሻሻያ ያመጣል ብለው ያስባሉ ለሚለው ጥያቄ አቶ ገብሩ ምላሽ አላቸው።

"ካለን ልምድ ኢህአዴግ በቂና አጥጋቢ መልስ ሲሰጥ አላየንም፤ አሁን ካሉት እርምጃዎች የተነሳ ጨለምተኛ መሆን አልፈልግም። በተግባር የምናየው ይሆናል" ብለዋል።