በደሴ ከተማ የሸዋበር መስጂድ ላይ በደረሰ ጥቃት 11 ሰዎች ተጎዱ

ደሴ ከተማ ፒያሳ አካባቢ

ትናንት ማታ በደሴ ውስጥ በሚገኘው በሸዋበር መስጂድ ቁርዓን በመቅራት ላይ በነበሩ ግለሰቦች ላይ በተፈፀመ ጥቃት 11 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።

የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መንግሥቱ ወርቁ እንደነገሩን አንድ ሰው ለህይወታቸው የሚያሰጋ ባይሆንም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ቀላል ጉዳት እንዳጋጠማቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሦስት የሚሆኑ ሰዎች ጭንቅላታቸው ላይ መፈንከት እና የተለያየ አካላቸው ላይ ቅጥቃጤ መድረሱን የሚናገሩት ዶ/ር መንግሥቱ ጉዳታቸው ቀላል በመሆኑ ማታ ማስታገሻ ተሰጥቷቸው ዛሬ ማለዳ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

"የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ አልተጠናም" ዶክተር አሰፋ ባልቻ

በደብረማርቆስ 'ባለስልጣኑ አርፈውበታል' የተባለው ሆቴል ጥቃት ደረሰበት

ታላቁ አንዋር መስጊድ ከእሳት ተረፈ

ሀጂ ሰዒድ እንድሪስ ሸዋበር አካባቢ የሚኖሩ እና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ የደሴ ከተማ ነዋሪ ናቸው።

እንደእርሳቸው ከሆነ ጥቃቱ በእርሳቸውና በሌሎች ላይ የደረሰው በመስጂድ ቁርዓን በመቅራት ላይ እያሉ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሀጂ ሰዒድ እንደሚሉት ባለፉት ሰባት ዓመታት በአስተምህሮ ልዩነት ምክንያት ከመስጂድ ርቀው እንደነበር የሚናገሩ ሙስሊሞች ዕረቡ ዕለት ተሰባስበው ጉዳያቸውን መወያየታቸውን ያስታውሳሉ።

በወቅቱም መንግሥት አሁን በፈጠረላቸው ዕድል ተጠቅመው በመስጂድ ቁርዓን ለመቅራት እንደተነጋገሩ ከማንኛውም ወገን ትንኮሳ ቢመጣ በትዕግስት በማሳለፍ ለማነጋገር በመወሰን ኮሚቴ መምረጣቸውን ያስታውሳሉ።

በዚህ መልኩ ሐሙስ ዕለት ትምህርታቸውን ጀምረዋል። ሀጂ ሰዒድ እንድሪስ አረብኛውን ሲያነቡ ሼህ መሀመድ ኑር እየተረጎሙ በሸዋ በር አካባቢ የሚገኙ ወንድሞችን ማስተማር መጀመራቸውን ሀጂ ሰዒድ ይናገራሉ።

ጨምረውም ቅዳሜ ዕለት በመስጂዱ ውስጥ ትምህርታቸውን የቀጠሉ ቢሆንም እሁድ ዕለት ግን የመስጂዱ አስተዳደር ማስተማር አይቻልም የሚል ማስታወቂያ መለጠፉን ያስታውሳሉ።

በወቅቱ የመረጧቸው ኮሚቴዎች አስተዳደሮቹን ከመስጂዱ ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይፈልጉ፤ ፍላጎታቸው ቁርዓን መቅራት መማማር እንደሆነ ማስረዳታቸውን ይናገራሉ።

ሰኞ እለት ጠዋት ከመንግሥት እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እስከ ዙህር ሰላት ድረስ በሚገባ መወያየታቸውን ከዚያ በኋላም ቀበሌ 04 የሚመለከታቸውን አካላት ይዘው ውይይት ማድረጋቸውን በመጨረሻም መግባባት ላይ መደረሱን ያስረዳሉ።

በዚህ ምክንያት ነበር ማታ ላይ የተለመደውን የመማማር ሂደት የቀጠልነው የሚሉት ሀጂ ሰዒድ፤ ነገር ግን ከኮምቦልቻ እና ሌሎች አካበባቢዎች የመጡ ሰዎች መረበሽ መጀመራቸውን ይናገራሉ። ሀጂ ሰዒድ እርሳቸው ደጋግመው አላህን ፍሩ በማለት መለመናቸውን ያስታውሳሉ።

ትምህርቱ እየቀጠለ እያለ ግን እዚህ መማማር እንደማይችሉ እንደተነገራቸውና በድጋሚም ከአስተዳደሩ እና ከመንግሥት አካላት ጋር ተነጋግረው እንደተፈቀደላቸው በመንገር ወደ ትምህርታቸው መግባታቸውን ያስታውሳሉ።

በኋላም አንድ ጥቁር ሸሚዝ የለበሰ እና ኮፊያ ያደረገ ፊቱ የማይታይ ወጣት ድንገት ከሚማሩት መካከል በመነሳት "ይቁም ይቁም ይቁም" በማለት መጮሁን ያስታውሳሉ።

ይኼኔ ተማሪዎቹን አረጋግተው የማስተማር ሥራቸውን ቢቀጥሉም ስጋት ስለገባቸው አምስት ልጆችን መርጠው አካባቢውን እንዲቃኙ መላካቸውን ይናገራሉ።

ከዚህ በኋላ "አላሁ ወክበር በለው" በማለት በድምፅ ማጉያ መናገራቸውን እና ጥቃቱ እንደተፈፀመባቸው ያስረዳሉ።

እንደ ሀጂ ሰኢድ ከሆነ አንድ ገጀራ፣ ድንጋይ እንጨት መፍለጫ 3 ፌሮ ብረት እንዲሁም ድንጋይ መስጂዱ ውስጥ ማየታቸውን ይናገራሉ።

በወቅቱ መስኪድ ውስጥ 42 ሰዎች መያዛቸውን ቀሪዎቹ ከመስጂድ ውጭ ተይዘው አሁን 55 ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ገልፀውልናል።

የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር ጌታቸው ሙስዬ በነበረው ግጭት በጥርጣሬ የተያዙት 56 ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ዛሬ ከተለያዩ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ