በኬንያ ናይሮቢ ለመንገድ ግንባታ የበርካቶች ቤት ፈረሱ

ካትሪን ካሚሪ (ግራ) እና ሜርሲ ዋንጂኩ (ቀኝ) ንብረታቸውን ሲሰበበስቡ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ መንግስት አካባቢው ለመንገድ ዝርጋታ ይፈለጋል ብሏል

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የተጨናነቀ መንደር ኪቤራ በመላው አፍሪካ ከሚገኙ መሰል መንደሮች ሰፊው መሆኑ ይነገርለታል። ኪቤራ የብዙ ሺዎች ቀዬም ነው።

የኬንያ መንግስት 20 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ መንገድ ለመገንባት አካባቢው ስለሚያስፈልግ ነዋሪዎቹ ጓዛቸውን ጠቅልለው እንዲወጡ ያሳሰበው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

የኪቤራን ቤቶች ለማፈራረስ ትልልቅ ደምሳሽ መኪኖች ወደ አካባቢው ሲያቀኑ ነዋሪዎቹ በየጥጉ ሆነው በሀዘኔታ ከመመልከት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።

በእርግጥ የኪቤራ ነዋሪዎች የመንገድ ዝርጋታውን በመቃወም ከአንዴም ሁለቴ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል። ሆኖም የሚሰራው መንገድ የኬንያን የመንገድ መጨናነቅ ይቀንሳል ስለተባለ ሰሚ አለገኙም።

በኬንያ በርካታ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች ተቃጠሉ

ኬንያ ሺሻን አገደች

ኬንያ ሳተላይት ልታመጥቅ ነው

ትላንት አንዳንድ የኪቤራ ነዋሪዎች ያላቸውን ንብረት እየሸከፉ እሮሯቸውን ያሰሙ ነበር።

የ30 ዓመቷ ጃኩሊን አንዜሞ የሶስት ልጆች እናት ናት። የመኖሪያ መንደሯ መፍረስ የሚያሳድርባትን ተጽእኖ ቶምሰን ሮይተርስ ለተባለ ተቋም እንዲህ ተናግራለች።

"ተወልደን ያደግነው እዚህ ነው። የተማርነው፣ ጎጆ የቀለስነውም እዚሁ ነው። ታዲያ አሁን ወደየት እንሂድ?"

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ መንግስት አካባቢው ለመንገድ ዝርጋታ ይፈለጋል ብሏል

ጃኩሊን ብቻ ሳትሆን አርተር ሻኩዎራም ከሁለት አሰርታት በላይ የኖረበት ቤቱ ሲደመሰስ በሀዘኔታ ከመመልከት ውጪ አንዳች ነገርም ማድረግ አልቻለም።

"ያለኝን ንብረት ጎረቤቶቼ ጋር አስቀምጫለሁ። ባለቤቴና ልጆቼ ለጊዜው ወንድሜ ጋር ይቆያሉ። ከዚህ በኃላ እንዴት ኑሮዬን እንደምገፋ እንጃ" ሲል ግራ መጋባቱን ይገልጻል።

አርተር መንገድ መሰራቱን ባይቃወምም ውሳኔው የኪቤራ ነዋሪዎችን ታሳቢ ማድረግ ነበረበት ይላል።

የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ እንዳስነበበው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የህጻናት ማቆያም ፈርሷል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ አምንስቲ ኢንተርናሽናል የቤቶቹን መፍረስ ተቃውሟል

የመብት ተሟጋቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የነዋሪዎቹን መፈናቀል ቢቃወምም የኬንያ መንግስት የነዋሪዎቹ ሰፈራ በህገ ወጥ ነው ብሏል። ተቋሙ ህጻን፣ ወጣት፣ አዛውንት ሳይል የበርካቶችን ህይወት ያመሰቃቀለውን የመንገድ ዝርጋታ ተቃውሟል።

የኬንያ ሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ዳይሬክተር ኢሩንጉ ሀውተን እንደሚለው የአካባቢው ነዋሪዎች በፈረሰባቸው ቤት ምትክ ካሳ ይከፈላቸዋል ቢባልም ቀድሞ መንደሩ መፍረሱ መንግስት ቃሉን ሊያጥፍ እንደሆነ ያሳያል።

የኬንያ መንገዶች ባለስልጣን በኢሩንጉ ንግግር ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም። ሆኖም ለነዋሪዎቹ ምትክ መኖሪያ እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ