በደምቢ ዶሎ በተፈፀመ ጥቃት አንዲት ነፍሰጡር ስትሞት 4 ሰዎች ቆሰሉ

ምዕራብ ኦሮሚያ

በምዕራብ ኦሮሚያ ደምቢ ዶሎ ውስጥ ባልታወቁ ኃይሎች በተፈፀመ ጥቃት የአንዲት ነፍሰጡር ህይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች በጥይት መቁሰላቸውን የአካባቢው አስተዳዳሪዎችና የሆስፒታል ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

ወ/ሮ ብርሃኔ ማሞ ከእርግዝናቸው ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ክትትል አንዲያገኙ ከሰዮ ወረዳ ወደ ደምቢ ዶሎ ሆስፒታል እንዲሄዱ ይደረጋል።

ወ/ሮ ብርሃኔ በአንድ ባጃጅ ከሌሎች 5 ሰዎች ጋር በመሆን ጉዟቸውን ወደ ደምቢ ዶሎ ያደርጋሉ። ከምሽቱ 5፡30 አካባቢ ደምቢ ዶሎ ከተማ ሲደርሱ ድንገት ተኩስ ተከፍቶ የወ/ሮ ብርሃኔ ህይወት ሲያልፍ አራቱ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ደምቢ ዶሎ ሆስፒታል እንደደረሱ የሆሰፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከማል ሂርኮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ጥቃት ጀርባ ያለው ማን ነው?

በደሴ ከተማ የሸዋበር መስጂድ ላይ በደረሰ ጥቃት ሰዎች ተጎዱ

በጎባው ግጭት የስድስት ሰዎች ሕይወት ጠፋ

ከወ/ሮ ብርሃኔ ጋር በባለ ሦስት እግሯ ተሽከርካሪ (ባጃጅ) አብረው ወደ ሆስፒታል ሲጓዙ የነበሩት ወ/ሮ ዘሃራ ከድር እጅ እና እግራቸው በጥይት ቢመታም ህይወታቸው ተርፋለች። ወ/ሮ ዘሃራ ''ብርሄኔ የመውለጃ ቀኗ ደርሶ ነበር። ሜጢ ወደ ሚባል የጤና ኬላ ስንወስዳት ይህ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ወደ ደንቢ ዶሎ ውሰዷት ሲሉን ባጃጅ ይዘን ወደ ደምቢ ዶሎ መጣን። ደምቢ ዶሎ ከተማ ከደረስን በኋላ ማን እንደሆነ ሳናውቅ ተኩስ ተከፈተብን'' ሲሉ ይናገራሉ።

የቄለም ወለጋ ምክትል አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ቢሮ ሃላፊው አቶ ጸጋዬ ዋቅጅራ ''ተኩስ ከፍቶ ግድያውን የፈጸመው ማን እንደሆነ በትክክል ማወቅ አልቻልንም። ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን እያጣራን ነው'' ይላሉ።

አቶ ጸጋዬ ጨምረው እንደተናገሩት ግድያውን የጸጥታ አስከባሪዎች እንደፈጸሙት እናውቃለን ይሁን አንጂ ''የአገር መከላከያ ነው፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ወይም ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ነው የሚለውን ማጣራት አለብን'' ብለዋል።

አንድ የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ አንደተናገሩት ''ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ወደ ባጃጁ ተጠግተው የፈጸሙትን ሲመለከቱ በመደናገጥ የባጃጁን ሹፌር ተጎጂዎቹን ወደ ሆስፒታል እንዲወስድ ትዕዛዝ ሰጡት'' ይላሉ።

''ወ/ሮ ብርሃኔ ጀርባቸውን ተመትው ነው የሞቱት'' የሚሉት የደምቢ ዶሎ ሆስፒታል ኦፕሬሽን ከፍል ሰራተኛ አቶ ዲሪባ አያና ናቸው። ''ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ነው እኛ ጋር የደረሱት። 30 ደቂቃ ቀደም ብለው ቢደርሱ ኖሮ ህይወታቸውን ማትረፍ ይቻለን ነበር'' ብለዋል አቶ ዲሪባ።

''በባጃጇ ውስጥ የነበሩት አብዛኛዎቹ የተመቱት ከደረታቸው በላይ ነው'' ሲሉም አቶ ዲሪባ ስለ ተጎጂዎቹ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ብርሃኔ እድሜያቸው ወደ 35 የሚገመት ሲሆን የስምንት እና የአምስት ዓመት ሴት ልጆች እናት ነበሩ።

የምዕራብ ኦሮሚያ የጸጥታ ጉዳይ

ከሳምንታት በፊት በነቀምቴ፣ በጊምቢ፣ ደምቢ ዶሎና በሌሎችም የምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግድያና የአካል ማጉደል ጥቃቶች ተፈፅሟል። ቤቶች ተቃጥለዋል መንገዶችም ተዘግተው ነበር።

ከሦስት ሳምንት በፊት የኦሮሚያ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ባይሳ ኩማ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ግድያ መፈፀሙን፣ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ተኩስ የመክፈትና መሳሪያ የመንጠቅ እንዲሁም ቦምብ መወርወርና ሌሎችም ዓይነት ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ያነጋገርናቸው ሌሎች ሰዎች ጥቃቱን የፈፀመው አካል ያልታወቀ ነው ቢሉም አዲስ ቡድን ሳይሆን፤ ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ስም አካባቢው ላይ ሲንቀሳቀስ የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ ግን ከጥቃቱ ጀርባ ኦነግ እንደሌለበት ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ