ካለሁበት 41: አብዱልራሂም ከባሌ ገበሬዎችን እስከ ቻድ ሕዝቦች የመብት ጥያቄ ሲል ብረት አንስቷል

አብዱራሂም አብዱልዓዚዝ

የፎቶው ባለመብት, አብዱራሂም አብዱልዓዚዝ

ስሜ አብዱልራሂም አብዱልዓዚዝ ይባላል። በባሌ ዞን ድሬ በምትባል ከተማ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደኩት። በእርግጥ በልጅነቴ በሐረር ዘለግ ላለ ጊዜ ተቀምጫለሁ።

ከአገር ሽሽቼ የወጣሁት በንጉሡ ዘመን ነበር።

ያኔ ባሌ ውስጥ የተጋጋለ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በጦርነቱ ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ተገድለዋል፤ በርካቶች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

በዚያን ወቅት ታዲያ ገና የ12 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ያም ኾኖ ዕድሜዬ ትግሉን ከመቀላቀል አልገደበኝም። በዚያን ወቅት የነበረውን ሥርዓት ለመጣል ነፍጥ አንስቼ ጫካ ገባሁ። ከዚያን ጊዜ በኋላ በሄድኩበት ሁሉ ትግል ይከተለኛል።

ያኔ ትግሉን ስቀላቀል የትግሉ መሪ ዝነኛው ጄነራል ዋቆ ጉቱ ነበሩ። በዚያ የተሟሟቀ ትግል ምክንያት በአገር ውስጥ ባሌ፣ ሐረር፣ ወለጋ እና አዲስ አበባ ተዟዙሪያለሁ። ከአገር ውጪ ደግሞ በሶማሊያ እና በሱዳን የትግል ስልጠናዎችን ወስጃለሁ።

ቻድ-ሊቢያ-ኔዘርላንድ

ከሱዳን በኋላ ቀጣዩ መዳረሻዬ ቻድ ነበር። በቻድ በስደት ላይ በነበርኩበት ወቅት የሊቢያ መንግሥት ኡራ የሚባሉ የቻድ ሕዝቦችን ይበድል ስለነበረ ይህን በመቃወም አሁንም ተመልሼ ወደ ትግል ገባሁ።

በትግል ላይ ሳለሁ በሊቢያ መንግሥት ተማርኬ ወደዚያው ተወሰድኩ። ሊቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ጨለማ በሆነ ጉድጓድ ውስጥ ታስሬ ቆይቼ ነበር። እጅግ መራራ ጊዜን ነበር ያሳለፈኩት።

ከተፈታሁ በኋላ በብዙ ጥረት ወደ አውሮፓ አቀናሁ፤ ወደ ኔዘርላንድ።

አሁን የምኖረው ናይሜጋን በምትባል የሆላንድ ከተማ ውስጥ ነው። እጅግ ውብ ከተማ ናት ታዲያ። የዚህ አገር ሰው ሲበዛ ሥራ ይወዳል።

በዚህም ምክንያት ለራሳቸው እንኳ የሚሆን ጊዜ የላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Abdulrahim Abdulraziz

የምስሉ መግለጫ,

በኔዘርላንድ ተወዳጅ ከሆኑ ምግቦች መካከል አንዱ የሆነው ''ኢስታንፖት''

በኔዘርላንድ ተወዳጅ ከሆኑ ምግቦች መካከል የኔ ምርጫ የሆነው ''ኢስታንፖት'' የሚባለው ምግብ ነው። ይህ ምግብ ከድንች እና ከካሮት የሚሠራ ሲሆን የኔዘርላንዶች ባህላዊ ምግብ ነው።

እዚህ ''ዋል'' የሚባል ሥፍራ መጎብኘት ያስደስተኛል። ይህ የወደብ ሥፍራ ሲሆን ሰዎች ከመርከብ ላይ ሲወርዱ፣ እንዲሁም መርከቦች ባህር ላይ ሆነው ከርቀት በማየት ነፍሴ ሐሴት ታደርጋለች።

ወደዚህ አገር በመምጣቴ የአእምሮ እረፍት ማግኘት ችያለሁ። ያም ኾኖ ግን ብቸኝነቱ ከባድ ነው። ሰዎች በአንድ አካባቢ ይኖራሉ እንጂ አይተዋወቁም።

የፎቶው ባለመብት, አብዱራሂም አብዱልዓዚዝ

የምስሉ መግለጫ,

ይህ ሥፍራ ገጠራማውን የትውልድ መንደሬን ይስታውሰኛል።

በምኖርበት ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ "ኦይ" የሚባል ልምላሜ ሥፍራ አለ። ይህ ሥፍራ ገጠራማውን የትውልድ መንደሬን ይመስለኛል። አካባቢው በተለያዩ ዓይነት ተክሎች የተሸፈነ ነው።

ወደዚህ አገር ስመጣ ከብዶኝ የነበረው የአገሬውን ባሕል እና የአኗኗር ዘይቤ መላመዱ ነበር። በተለይ በሙቀት ወቅት እርቃናቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ስመለከት በጣም እደነግጥ ነበር።

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦