የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥይት ተመተው መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው ነው ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ዘይኑ ጀማል አስታወቁ።

ኮሚሽነሩ ጨመረውም እንደተናገሩት ከኢንጂነሩ አስክሬን ጎን ኮልት ሽጉጥ መገኘቱን ገልጸዋል።

ዝርዝር የአሟሟታቸውን ሁኔታ በተመለከተ ፖሊስ ምርመራውን እያካሄደ እንደሆነ እና በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞችን እና ምስክሮች ላይ ምረመራ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ መኪናቸው ውስጥ ባልታወቀ ምክንያት ህይወታቸው አልፎ መገኘቱ ይታወሳል።

ሐሙስ ሐምሌ 19/2010 ዓ.ም ጠዋት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ አደባባይ የሰሌዳ ቁጥሯ ኢቲ ኤ 29722፣ ላንድክሩዘር ቪ8 መኪናቸው ውስጥ ተገኘ የተባለው አስከሬን ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የስነ-ምረዛ እና አስክሬን ምርመራ ክፍል ተወስዶ መምርመራ እየተደረገለት ነው።

በአካባቢውም ፖሊስ ተሰማርቶ ምርመራ እያደረገ ሲሆን፤ ለሞታቸው ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

በአካባቢው የሚገኙት የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም መኪናቸው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገለት መሆኑና ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው እንዳሉ ገልጸዋል።

በትናንትናው ዕለት ቢቢሲ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ኢንጅነር ስመኘውን ባነጋገረበት ወቅት ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልጸው ነበር።

ኢንጅነር ስመኘው ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ በአካል ተገኘተን መመልከት እንደምንችል እና ከእሳቸውም ግድቡን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት በመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል እንድናቀርብላቸው ጠይቀውን ነበር።

የድምፅ መግለጫ,

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኢንጂነር ስመኘው ሞት የተሰማቸውን ከፍ ያለ ድንጋጤና ሐዘን በልዩ ረዳታቸው በኩል ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ከሰዓታት በፊት በትዊተር ገጻቸው እንደጻፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜናውን የሰሙት አሜሪካ ከደረሱ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሟች ቤተሰቦችና ወደጃች መጽናናትን ተመኝተዋል።

የኢንጅነር ስመኘው ሞት ከተሰማ በኋላ በርካቶች ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው። የኢህአዴግ ምክር ቤትም ባወጣው የሃዘን መግለጫ ''ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን እንዲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነትንና አደራ ለመወጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት አገልግለዋል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጨማሪ በሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦችም አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡'' ያለ ሲሆን ምክርቤቱ ጨምሮም፤ ''ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም ትጋታቸውና ጽናታቸው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ታትሞ የሚኖር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥትም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሚያደርጉትን ርብርብ በማጠናከር የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ህልምና ራዕይ ዕውን ያደርጋሉ'' ብሏል በመግለጫው።

የኢንጂነሩን ሞት ተከትሎም የተቆጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ''ኢትዮጵያ ነጻ ትውጣ፣ ፍትህ ለኢንጂነር ስመኘ'' የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ማናቸው?

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጎንደር ማክሰኚት በ1957 ዓም ተወልዱ። ኢንጂነሩ በ1970ዎቹ መጨረሻ እና 80ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በቀድሞው ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የቴክኒክ ስልጠና ማዕከል ውስጥ ተማሪ ሆነው መጡ። ከዚያም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተመረቁ በኋላ እዚያው ማስተማር ጀመሩ።

መምህር ሆነው የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ በተፈጠረ አለመግባባት መሥሪያ ቤቱን ለቅቀው የወጡ ሲሆን፤ ሲቪል ኢንጂነሪንግ አጥንተው ዳግመኛ በድርጅቱ ውስጥ ተቀጠሩ። ከዚያም በኋላ የጊቤ አንድ ምክትል ፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን በተጨማሪም የጊቤ ሁለት ደግሞ የፕሮጀክቱ ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል።

ኢንጂነር ስመኘው የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ከሃገር ውጪ ካናዳ ውስጥ እንደሚገኙ ለቤተሰባቸው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በ2007 ዓ.ም የበጎ ሰው ለተባለው ሽልማት መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን እስከ ህልፈተ- ህይወታቸው ድረስም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የፕሮጀክት ኃላፊ በመሆን ለሰባት ዓመታት ያህል ሲሰሩ ቆይተዋል።