አዲሱ አየርላንዳዊው ሙሽራ በግሪክ ሰደድ እሳት ምክንያት ህይወቱን ማጣቱ ተነገረ

ብራያንና ባለቤቱ ዞዊ

የፎቶው ባለመብት, Rebecca Burrell

አዲሶቹ ሙሽሮች ብራያንና ዞዊ ድንቅ የፍቅር ጊዜን ለማጣጣም በማሰብ ነበር በግሪክ ጫጉላቸውን ለማሳለፍ የተገኙት። ነገር ግን ግሪክ በእሳት ሰደድ ስትለበለብ እና በርካቶች ቤት ንብረታቸው የእሳት እራት ሲሆን እነርሱም ህይወታቸውን ለማትረፍ ተያይዘው መሮጥ ጀመሩ።

ዙሪያቸውን ከቧቸው ከሚምዘገዘገው የእሳት ሰደድ ለማምለጥ ሲሮጡ ግን ተለያዩ። ከዚህ በኋላ ነው የእርሱ መሞት የተነገረው። የባልና ሚስቱ ቤተሰቦችም በጋራ በመሆን መሞቱን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ቤተሰቦች በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይም በጥልቅ ማዘናቸውን ገልፀዋል።

እንዲሁም ባለቤቱ ዞዊ በቅጡ ማዘን እንድትችል ጊዜ እንዲሰጧት ጠይቀዋል።

በግሪክ የአየርላንድ አምባሳደር የሆኑት ኦርላ የብራያንን መሞት አረጋግጠው የተሰማቸውን ሀዘንና ለቤተሰቡ መፅናናትን ተመኝተዋል።

በግሪክ ሰደድ እሳት ከ 70 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በርካታ የግሪክ መንደሮች በሰደድ እሳቱ ተበልተዋል፤ የመዝናኛ ስፍራዎች ወድመዋል።

የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፐራስ የሶስት ቀን የሐዘን ቀን ያወጁ ሲሆን ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፖላንድ እና ፈረንሳእ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎችንም ድጋፎችን አድርገዋል።

ስፔይን እና ቆጵሮስ የድጋፍ እጃቸውን ከዘረጉ ሀገራት መካከል ይገኙበታል።