የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞትን ተከትሎ በጎንደር ረብሻ ተከሰተ

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ህልፈት ተከትሎ ዛሬ በጎንደር ከተማ ረብሻ እንደነበር የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባበል ለቢቢሲ ገለጹ።

አለመረጋገቱ "ለኢንጂነሩ ሞት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለፍርድ ይቅረቡ" በሚል የተቀሰቀሰ ሲሆን ትላንት አንድ የሠላም ባስ አውቶብስ መቃጠሉን ከንቲባው ገልጸዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ የተጀመረው ተቃውሞና ግርግር ለሰዓታት ዘልቋል። ሰልፉን ባካሄዱ ሰዎች ላይም ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱም ተነግሯል።

ቢሆንም ግን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ሰልፉ በተካሄደበት አካባቢ አንድ ሱቅ ላይ በድንጋይ ጉዳት ደርሷል።

ስለኢንጂነር ስመኘው አሟሟት እስካሁን ምን እናውቃለን?

"የእሱ አባት ኩራዝ የላቸውም፤ እሱ ግን ኢትዮጵያን ሊያበራ ነው የሞተው"

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሕይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው ነው፡ ፌደራል ፖሊስ

የአሜሪካ ኤምባሲም ዜጎቹ ወደ ጎንደር እንዳይሄዱ የጉዞ እገዳ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።

ከንቲባው በበኩላቸው "ያልተፈቀደና ባለቤት የሌለው" ካሉት የዛሬው ሰልፍ ጀርባ ያሉት ሰዎች እንዳልታወቁ ገልጸውልናል።

"ትላንት የነበረው ሁኔታ ኢንጂነር ስመኘው እዚሁ አካባቢ ተወልዶ ከማደጉ ኣንጻር በመሞቱ ሀዘን ለመግለጽ እንጂ ሌላ አጀንዳ አልነበረውም። ሆኖም አጋጣሚውን በመጠቀም ጎንደርን ለመበጥበጥ የሚፈልጉ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል" ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አለመረጋጋቱን ተከትሎ ሰዎች እንደተጎዱ፣ ንብረትም እንደወደመ እንዲሁም የእለት ከእለት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

የተጎዳ ሰው ስለመኖሩና የንብረት ውድመት ስለመድረሱ ከንቲባውን ስንጠይቃቸው የተጎዳ ሰው እንደሌለና ከተሰበረው ሱቅ ውጪ ሌላ ንብረት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጸውልናል።

ከንቲባው ከሰዓት በኋላ ነገሮች መረጋጋታቸውን ገልፀው ረብሻው የከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ እንደማያሳድርም አክለዋል።

Image copyright Getty Images

ትላንት ከሰዓት የኢንጅነሩን አባት፣ እህት፣ የአክስት ልጆችና ሌሎችም ቤተሰቦች በመቀላቀል ሀዘናቸውን የገለጹ የከተማዋ ነዋሪዎች ነበሩ። ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከልም ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑ የኢንጂነሩን ቤተሰቦቹን በማጀብ ሀዘናቸውን ያስተጋቡም ነበሩ።

ትላንት አመሻሽ ላይ በዛሬው እለት በጎንደር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ የሚያቀርብ በራሪ ወረቀት የተበተነሲሆን፤ ከንቲባው እንደሚሉት በራሪ ወረቀቱን ያሰራጩ ሰዎች ማንነት እስካሁን አልታወቀም።

ከንቲባው ሰልፉን የጠሩትንና ያካሄዱትን ሰዎች "ጎንደርን ወደቀደመው አለመረጋጋት ለመክተት ሞክረዋል" ቢሉም ለኢንጂነር ስመኘው ህልፈት ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለፍርድ ይቅረቡ የሚል መልዕክትን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።

የአሜሪካ ኤምባሲን ማስጠንቀቂያ በተመለከተ ዛሬ ጠዋት የኤምባሲው መግለጫ ቢደርሳቸውም የከተማዋን መረጋጋት በማየት እገዳው እንደሚነሳ ተስፋ እንደሚያደርጉ አቶ ተቀባ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በተፈጠረው አለመረጋጋት የከተማዋ የቱሪስተ ፍሰት ማሽቆልቆሉ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ