አንበሶችን ያባረረው ወጣት ምን አጋጠመው?

ሪቻርድ ቱሬሬ እንስሳቱን ጋር
አጭር የምስል መግለጫ ሪቻርድ ቱሬሬ እንስሳቱን ከእንበሳ ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ ሲያፈልቅ ገና ታዳጊ ነበር።

''አንበሳ እወዳለሁ ፤ የማልወድበት ምክንያት አይታየኝም''

''ላሞቼ ደህና ከሆኑና ከተጠበቁልኝ ከአንሰቦቹ ጋር ያለምንም ችግር መኖር እንችላለን።"

ይህን ከአንድ የኬንያ ማሳይ እረኛ መስማት ያልተመለደ ነገር ነው።

ዋነኛው ሥራቸው በማናቸውም መንገድ ቢሆን ላሞቻቸውን ከጥቃት መከላከል ነው።

የ18 ዓመቱ ሪቻርድ ቱሬሬ ግን እንደማንኛውም የማሳይ እረኛ አይደለም።

በወቅቱ ቤተሰቦቹ በአንድ ሳምንት ከ9 ያላነሱ ከብቶቻቸው በአንበሶች ተበልተውባቸው ስለነበር የ11 ዓመት ልጅ እያለ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ አንበሶችን ከከብቶች በረት የሚያባርር መብራት ፈጠረ።

የዕለት ከዕለት ኑሮን የሚለውጡ ፈጠራዎች

እያንዳንዱ ላም እስከ 1000 ዶላር ዋጋ ያሚያወጣ በመሆኑ ቤተሰቦቹ ኪሳራውን መቋቋም ተስኗቸው ነበር።

''በከብቶቻችን ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች መጠነ ሰፊና በየቀኑ የሚያጋጥሙን ነበሩ" ይላሉ የሪቻርድ እናት ቬሮኒካ። ''ከመብራቶቹ በኋላ ግን ከአንበሶቹ ጋር ምንም ችግር አልገጠመንም።''

ሪቻርድ ይህንን ፈጠራውን ስኬታማ ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ ፈጅቶበታል። በመጀመሪያ ሰው የሚመስሉ ቅርጾችን በአካባቢው ቢያቆምም አንበሶቹ ከቁብ ሳይቆጥሩት ቀሩ። በመቀጠል ደግሞ አንበሶቹ የእርባታውን የውስጥ ክፍል ማየት እንዳይችሉ ጥቁር መከለያ ቢሰራም የላሞቹን ጠረን ከማሽተት አላገዳቸውም።

አንድ ቀን ግን የእጅ ባትሪ ይዞ በተንቀሳቀሰበት ምሽት አንበሶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማጥቃት ሳይመጡ ቀሩ።

ሪቻርድም የእጅ ባትሪውን የሚንቀሳቀስ በማስመሰል ስላዘጋጀው ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አጥቶ ከመጠበቅ የገላገለውን 'ላየን ላይትስ' መብራትን ሰራ።

አጭር የምስል መግለጫ አንበሶች በርካታ ከብቶችን ይገድላሉ

ራስን ማስተማር

"ነገሮችን በመሰባበር ነው ስለ ኤሌክትሮኒክስ መማር የጀመርኩት" ይላል ሪቻርድ። ''የእናቴን አዲስ ሬድዮ ሰብሬ በጣም ተናዳ ልትገድለኝ ደርሳ ነበር።''

በእያንዳንዱ ስሪት ላይ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እያደረገ አሁን 'ላየን ላይትስ' በሪቻርድ ማህበረሰብና በሌሎች አካባቢዎች በ750 መኖሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። "ሰዎች እንዴት እንደሚሰሩ በውል ስለማያውቁ ብዙ ጊዜ መብራቶቹን ለመጠገን እጥራለሁ'' ብሏል ሪቻርድ።

'' ራሳቸው ለመጠገን ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን ሳይ አሰራሩን አውቶማቲክ የማድረግ ሃሳብ አመነጨሁ።

'ላየን ላይትስ 2.0' ን ለመስራት 200 ዶላር ወይም 150 ፓውንድ ይፈጃል። ብዙ ጊዜ ከዚህ ወጪ ግማሹ መንግሥታዊ ባልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ቀሪው ደግሞ በከብት አርቢዎቹ ይሸፈናል።

ይህ ስሪት 16 የተለያዩ የመብራት አማራጮች አሉት። የሪቻርድ የመጨረሻው የተሻሻለ ፈጠራ በደመና ምክንያት የፀሐይ ኃይል አቅም ሲቀንስ ቤት ውስጥ የተሰራ ለቀናት የሚቆይ የነፋስ ማጦዣ አለው።

አጭር የምስል መግለጫ ሪቻርድ ብዙ ጊዜ እራሱ እየሄደ መብራቶቹን መጠገን አለበት

የላም ባንኮች

ሪቻርድ የሚኖርበት ማህበረሰብ የሰዎችና የዱር እንስሳት ግጭት በተደጋጋሚ የሚከሰትበት ነው። በናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክና በኪቴንጌላ ከተማ መካከል የሚገኘውን ''የማህበረሰቡ መሬት" ከፓርኩ የዱር እንስሳት የሚለየው አነስተኛ ወንዝ ብቻ ነው።

ሁልጊዜ ማታ ማታ የዱር እንስሳትና የሜዳ አህያ ለምለም የግጦሽ መሬት ፍለጋ መሬታቸውን ያቋርጣሉ፤ አንበሶችም ወዲያው ይከተላሉ።

''አንበሶች ትልቅ ችግር ናቸው። ለእነርሱ ላሞችና በጎችን መግደል በጣም ቀላል ነው፤ በተለይ ደግሞ በማታ '' ይላሉ የማሳይ ማህበረሰብ ሰባኪና አርብቶ አደሩ ሬቨረንድ ካልቪን ታፓያ። "ሆኖም ላሞችና በጎች ለእኛ ባንኮቻችን ናቸው፤ ገንዘባችንን የምናከማቸው እነርሱ ጋር ነው።"

ሪቻርድ እስካሁን ከመንግሥት ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ባያገኝም የእርሱ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ብሄራዊ ፓርኮች ለሚያስተዳደረው የኬንያ የዱር እንስሳት አገልግሎት እገዛ እያደረገ እንደሆነ ያስባል።

ድርጅቱ እንደሚለው ላለፉት አስር ዓመታት ኬንያ በየዓመቱ 100 አንበሶችን እያጣች ሲሆን አሁን በዱር 1700 የሚሆኑት ብቻ ቀርተዋል። ከእነዚህ ሞቶች መካከል የተወሰኑት በሰዎች ምክንያት የተከሰቱ ናቸው።

አጭር የምስል መግለጫ የሪቻርድ ቱሬሬ ሃሳብ ዓለምን አዳርሷል

በቀል

በአውሮፓውያኑ 2012 ሁለት ሴት አንበሶችና ሁለት ደቦሎች በኪቴንጋ መኖሪያ ቤቶችን በመውረራቸው ግር ብለው በወጡባቸው ሰዎች ተገድለዋል ። የሪቻርድ 'ላየን ላይት' ልክ እንደርሱ ሁሉ ማህበረሰቡ ከብቶቹን እንዲከላከል እስካስቻለው ድረስ አንበሶችንም ከሰው ጥቃት ይታደጋቸዋል።

''ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ከበፊቱ ይልቅ ለበቀል ተብለው የሚፈጸሙ የአንበሶች ግድያ ተበራክቷል'' የዱር እንስሳት ባለሙያዋ የአፍሪካ ጥበቃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሉሲ ዋሩይነጊ አንደሚናገሩት።

''ለማሳዮችም ሆነ ለዱር እንስሳቱ የቀረው መሬት አነስተኛ በመሆኑ ከበፊቱ ይልቅ አሁን ተቀራርበዋል"

"አሁን የተጎዱትን የሚደግፍ አማራጭ ስርዓት አልተዘረጋም፤ 'ላየን ላይትስ' እንደሞከረው በአንበሶችና በሰዎች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት ለመከላከል እንኳ ጥረት አልተደረገም።"

በ2014 የኬንያ መንግሥት በሰዎችና በዱር እንስሳት መካከል በሚፈጠር ግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን የካሳ ተጠቃሚ የሚያደርግ ህግ አውጥቶ ነበር። ይሁንና በተግባር የሚካሱት ጥቂት ክስተቶች ብቻ በመሆናቸው አሁንም ጥያቄዎች እንደተከማቹ ናቸው።

''የእንስሳት፣ የንብረትና የሰብል ካሳን ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልቻልንም ምክንያቱም ገና በፓርላማ ያልጸደቁ መመሪያዎች አሉ'' ብለዋል በናይሮቢ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የማሀበረሰብ ጠባቂ፡፡

አጭር የምስል መግለጫ ሪቻርድ ቤት ውስጥ ያገኛቸው የነበሩ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ይገጣጥም

የሪቻርድ የፈጠራ ሥራ በብዙ መልኩ ህይወቱን ቀይሮታል። በናይሮቢ በሚገኝ ስመ-ጥር ትምህርት ቤት በነጻ የመማር ዕድልም አስገኝቶለታል። ቻይናዊውን የአሊባባ መስራች ጃክ ማ እንዲያገኝው ተጋብዞ ለክብሩ የተዘጋጀውን ትምህርት ተከታትሏል።

እርሱም በኬንያ ስመ-ጥር ሆኗል። እስከ አርጀንቲናና ህንድ ድረስ ያሉ ሌሎች ማህበረሰቦችም የእርሱን የፈጠራ ውጤት መሰረት አድርገው የተሰሩ መብራቶችን ይጠቀማሉ።

ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል

የሪቻርድ ሃሳብ አድማስ ቢሻገርም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አንደ አንድ ወጣት የፈጠራ ሰው የሚደረግለት ድጋፍም ሆነ የ'ላየን ላይትስ' መብራት አፈጻጸም ቀንሷል። ኬንያ እንደእርሱ ላሉ ወጣት የፈጠራ ሰዎች ከዚህ የተሻለ ድጋፍ ማድረግ እንደምትችል ያምናል።

"በኬንያ ከእኔም የተሻለ አስደናቂ ሃሳቦች ያሏቸው ብዙ ወጣቶች አሉ፤ የሚፈልጉት ድጋፍ ብቻ ነው'' ብሏል ሪቻርድ ።

"ይህ ሃሳብ በጣም አሪፍ ነው፤ 'የኬንያን ብሎም የዓለምን ማህበረሰብ እንዲያግዝ እናሳድገው' የሚላቸው ሰው ይፈልጋሉ።"

አጭር የምስል መግለጫ ሪቻርድ ቱሬሬ የፍየሎቹን ደህንነት መጠበቅ ይፈልጋል።

''እንደ'ላየን ላይትስ' ያሉ ፈጠራዎች ለኬንያ ብቻ አይደለም የሚያስፈልጉት" ይላሉ ሉሲ ዋሩይነጊ። "የሰብዓዊ ልማት በመላው ዓለም በፍጥነት እያደገ በመሆኑ መንግሥታት ከዱር አራዊት ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት የተገደዱ ማህበረሰቦቻቸውን ማገዝ አለባቸው።"

"መንግሥታት የፈጠራ ሰዎች ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሃሳቦችን እንዲያካፍሉ መድረኮችን ማመቻቸት አለባቸው'' ሲሉ ያክላሉ። ''እነዚህን ሃሳቦች ወደ ንግድ ሥራ በማሳደግ እንደ ሪቻርድ ያሉ ሰዎች ማህበረሰባቸውን በመደጎም እነርሱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ።''

ሪቻርድ እንደ 'ላዮን ላይትስ' ፈጣሪነቱ በአግባቡ ተጠቃሚ ካልሆነባቸው ምክንያቶች መካከል፤ ምንም እንኳ በ15 ዓመቱ የኬንያ በዕድሜ ትንሹ የፈጠራ ባለቤት ቢሆንም ሃሳቡን በጊዜ አለማስመዝገቡ ነበር።

ይህንን ስህተት በድጋሚ እንደማይሰራ ይናገራል፤ አሁንም በርከት ያሉ የፈጠራ ስራዎቹ በሂደት ላይ ናቸው።

"ይህ ነው የምወደው ሥራ። ቴክኖሎጂ እወዳለሁ፤ እጆቼን መጠቀምና ተግባራዊ ሥራ ላይ መሳተፍም ያስደስተኛል፤ ወደፊት መራመድ እንድችል የሚያግዘኝም ይሄው ነው።"

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ይህ የአፍሪካ ዋነኛው የፈጠራ አካባቢ ይሆን?

ተያያዥ ርዕሶች