በሜክሲኮ አውሮፕላን ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ተከሰከሰ

የተከሰከሰ አውሮፕላን የሚያሳይ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Protección Civil Durango/Twitter

የምስሉ መግለጫ,

ወደ ዋና ከተማዋ ሜከሲኮ ሲቲ በረራ ሊያደርግ የነበረው አውሮፕላን 97 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።

በሜክሲኮ ዱራንጎ በምትባል ግዛት ውስጥ አንድ አውሮፕላን ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተከስክሶ በርካቶች ጉዳት ደረሰባቸው።

በአደጋው ህይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩን የግዛቷ አስተዳዳሪ ያረጋገጡ ሲሆን፤ በአውሮፕላኑ ላይ ከነበሩት 101 ሰዎች 85 የሚሆኑት ተጎድተዋል። ከተጎዱት ሁለቱ አደጋው ለህይወታቸው ያሰጋቸዋል ተብሏል።

የተጎዱት ግለሰቦች ስም እና ዜግነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

የበረራ ቁጥር AM2431 ከመካከለኛዋ ዱራጎን ግዛት በደቡብ አቅጣጫ ወደምትገኘው ዋና ከተማ ሜክሲኮ ሲቲ በረራ ሊያደርግ ነበር። አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ማኮብኮብ ከጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር።

የአየር ማረፊያው ተቆጣጣሪ እስካሁን ባለቸው መረጃ ለአደጋው መንስኤ ሊሆን የሚችለው መጥፎ የአየር ሁኔታ መሆኑን ገልጸዋል። ተቆጣጣሪው ጨምረው እንደተናገሩት በወቅቱ የነበረው በረዶ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ አውሮፕላኑ እንዲያርፍ አስገድዶታል። አደጋው የደረሰውም አውሮፕላኑን ለማሳረፍ ጥረት በተደረገበት ወቅት ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/KEVIN ALCANTAR DRONES DURANGO

የምስሉ መግለጫ,

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር

በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበር አንድ መንገደኛ አውሮፕላኑን ከፍተኛ ኃይል ያለው ንፋስ ሲመታው ተሰምቶናል ሲል ለአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

ከአደጋው በኋላ አየር ማረፊያው ተዘግቷል።

የተከሰከሰው ኢምብረየር 190 የተባለው አውሮፕላን ብራዚል ሰራሽ ሲሆን፤ አምራቾቹ አደጋውን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው እንደላኩ አስታውቀዋል።