«የሠራዊታችን አባላት በክብር ይሸኛሉ» አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ

የአርበኞች ግንቦት 7 አርማ

የፎቶው ባለመብት, AG7

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የትጥቅ ትግልን በማቆም ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ መወሰኑን ይፋ አደረገ።

ንቅናቄው በዋሺንግተን ዲሲ በጠራው በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ሐምሌ 21/2010 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ተከትሎ ከውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል።

የመጀመሪያው የውይይት አጀንዳ ሀገሪቱ ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ እና በመካሄድ ላይ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚመለከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆንበትን አግባብ የሚጠቁም እንደነበር ተወስቷል።

በዚህም መሰረት የንቅናቄው አመራሮች እና አባላት በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደሚጀምሩ ይፋ ተደርጓል።

በተጨማሪም በኤርትራ እና በሌሎች ቦታዎች ያሉትን የንቅናቄው ሠራዊት አባላትን በተመለከተ የንቅናቄው ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር ለማድረግ የዘገየበት ዋና ምክንያት የሠራዊቱ አባላት መፃኢ ሁኔታን ለመወሰን ውይይት በማስፈለጉ መሆኑን ጠቅሰው ሠራዊቱ «በክብር የሚሸኝበት» እና ወደ ሰላማዊ ኑሮ የሚመለስበት ሁኔታ እንደሚመቻች አብራርተዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ይሄ ውሳኔ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄንም (ዴምህትን) እንደማያካትት ተናግረዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ወደ ትጥቅ ትግል ካመራባቸው ምክንያቶች አንዱ በሀገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የሚያበቃ ተቋማዊ ዋስትና ያለመኖሩ ጉዳይ መሆን ያነሱ አንድ ጠያቂ አሁን ባለው ሀኔታስ ንቅናቄን በሀገር ውስጥ በሰላማዊ ሁኔታ የሚያታግሉ ተቋማት አሉ ብሎ ያምን እንደሁ ጠይቀዋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ «እኒህ ተቋማት ተገንበተው አልቀዋል በሚል ሳይሆን እኒህን ተቋማት ለመገንባት የሚደረገውን ሂደት ማገዝ አለብን በሚል ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው» ሲሉ መልሰዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጃቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ነበር። ንቅናቄው በቅርቡ ከሽብርተኛ መዝገብ ላይ ስሙ እንዲፋቅ የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።