ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

የፎቶው ባለመብት, BogasTube

ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ትላንት ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ከጥቂት ወራት በፊት ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልገው መገለጹ ይታወሳል።

የተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ሞት የተሰማው ወልዲያ አካባቢ ወደሚገኘው አርሴማ ጸበል ሄዶ ሳለ ነበር። የተዋናይ ፍቃዱ አስክሬን ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ይሸኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ከታዳጊነቱ አንስቶ ለጥበብ ፍቅር እጁን የሰጠው ፍቃዱ በተለይም የንጉስ ገጸ ባህሪ ተላብሶ በመተወን የሚያህለው የለም ይባልለታል።

"እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ. . . " የሚለውን የአጼ ቴዎድሮስ ንግግር ሲጀምር ተመልካቾች በዘመን ወደኃላ ሄደው የቴዎድሮስን ጀግንነት በእውንም እየተመለከቱ እስኪመስላቸው ይደመሙ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የመሪ ተዋናይነት ሚና ያገኘው በአባተ መኩሪያው "እሳት ሲነድ" ነበር። ከዛ በኋላ በበርካታ ቴአትሮች ላይ ተሳትፏል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጥበብ ቤቱ ከነበረው ብሔራዊ ቴአትር አይጠፋምም ነበር።

ፍቃዱ እጅግ ገናና ከሆነበት "ቴዎድሮስ" ቴአትር በተጨማሪ በ"ኤዲፐስ ንጉስ"፣ "ሐምሌት" እና "ንጉስ አርማህ" ተውኔቶችም እንደ ንጉስ ተጫውቷል።

አዲስ አባባ አራት ኪሎ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ፍቃዱ መነሻው ቴአትር ቢሆንም በተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎች፣ በፊልሞች እንዲሁም በማስታወቂያ ሥራዎቹ እና በሬድዮ ትረካዎችም ጭምር ይታወቃል።

ከተወነባቸው የቴሌቭዥን ድራማዎች መካከል "ባለጉዳይ"፣ "ያልተከፈለ እዳ"፣ "የአበቅየለሽ ኑዛዜ"፣ ''ገመና'' ይጠቀሳሉ። ማህበራዊ ትችት አዘሉ "ባለጉዳይ" በቴሌቭዥን ይተላለፍ በነበረበት ወቅት ተመልካቾች 'ብሶታችንን አደባባይ አወጣልን' ይሉ እንደነበር ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ራድዮ ይተላለፍ የነበረው "ከመጻሕፍት አለም" ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ትረካዎች በርካታ መጻሕፍት ላይ ህይወት ዘርቷል። "ሞገደኛው ነውጤ"፣ "ጥቁር ደም"፣ "ሳቤላ"፣ "ወንጀለኛው ዳኛ" እና "ግራጫ ቃጭሎች" ከተረካቸው መጻሕፍት መካከል ይጠቀሳሉ።

በአበራ ለማ የተጻፈው "ሞገደኛው ነውጤ" ላይ ያለው ነውጤ የተሰኘው ገጸ ባህሪ ከብዙዎች ሕሊና አይጠፋም። ብዙዎች ነውጤን ሲያስቡ ፍቃዱ ትውስ ይለቸዋል። የሀዲስ አለማየሁ "ወንጀለኛው ዳኛ"ም ፍቃዱ ከሚታወስባቸው ስራዎች ይገኝበታል።