የኃይለማርያም እና የመንግሥቱ ፎቶ ለምን በርካቶችን ግራ አጋባ?

ሃይለማርያም ደሳለኝ እና መንግሥቱ ሃይለማርያም Image copyright Hailemariyam Desalegn

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ብዙዎችን ግራ ያጋባውን ፎቶ ከፌስቡክ ገጻቸው ላይ አንስተውታል። ከሁለት ቀናት በፊት ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከለጠፉ በኋላ በርካቶች ፎቶውን ከአስተያየታቸው ጋር በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሲቀባበሉት ነበር።

ፎቶው የተነሳው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚምባብዌ የተካሄደውን ምርጫ ለመታዘብ የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድንን በመምራት ወደ ዚምባብዌ ካቀኑ በኋላ ነበር። ፎቶው በኢትዮጵያ ታሪክ ሁለት የቀድሞ መሪዎች አብረው ፎቶግራፍ ሲነሱ የመጀመሪያ በመሆኑ በበርካቶች ላይ ልዩ ስሜትን ፈጥሯል።

የቀድሞዎቹ መሪዎች ኃይለማርያም ደሳለኝና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተገናኙ

መንግሥቱ እና የኮሎኔል አጥናፉ ኑዛዜ

ለፍርድ የቀረቡ አፍሪካውያን መሪዎች

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ምን ተባለ?

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለምርያም ደሳለኝ ፎቶግራፉን ከፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከማጥፋታቸው ቀደም ብሎ ''ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ተገናኝቻለሁ። ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከተካሄደ በኋላ የቀድሞ የሃገር መሪዎች ለሃገር እድገት የተቻላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበርካቱ ማየት እመኛለው'' ብለው ነበር።

Image copyright Hailemariam Desalegn
አጭር የምስል መግለጫ ይህ የፌስቡክ ፖስት ከሃይለማርያም ደሳለን የፌስቡክ ገጽ ላይ ተሰርዟል

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከተነበቡ አስተያየቶች መካከል ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃያለማርያም ጋር ፎቶ መነሳታቸውን የተቃወሙ ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ፎቶውን የተመለከቱ ቀላል የማይባሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መንግሥቱ ወደ አገር ቢገቡ ደስታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ኮሎኔል መንግስቱ 'ስላደረሰው ጥፋት በህግ ሊጠየቅ ሲገባው እንዴት እውቅና ይሰጠዋል?' የሚል ቅሬታቸውን በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩ ነበሩ። አቤል አባተ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ''በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ይህ ሌላ ለውጥ ነው'' ያለ ሲሆን አወል አሎ ደግሞ፤ ይህ ፎቶግራፍ እጅጉን ግራ ያጋባል። መንግሥታችን ስለ ፍቅር እና መግባባት ማውሳቱ መልካም ሆኖ ሳለ ይቅርታ እና ምህረትን ግን ለሁሉም የሚሰጥ አይደለም ብሏል።

አንዲት ኤርትራዊት በትዊተር ገጿ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዘዳንት የሞቀ አቀባበል ሲያደርጉ 'እንዴት ከአምባገነን ጋር?' ሲሉ ብዙ ኤርትራውያን መቆጣታቸውን ከኃይለማርያምና ከኮሎኔል መንግስቱ መገናኘት ጋር አነጻጽራ ጽፋለች።

የሁለቱን የቀድሞ መሪዎች በጥምርት ፎቶ መነሳት አሳፋሪ፣ ያልተገባ ሲሉ የተቹ እንደሉ ሁሉ ባለፈው ዘመን ብዙ ጥፋት ያጠፉ ሰዎች ይቅር ተብለዋል ለምን የኮሎኔል መንግስቱ በተለየ መንገድ ይታያል ሲሉ የጠየቁም አሉ።

ይህ ፎቶግራፍ ለምን በርካቶችን አነጋገረ?

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የመሩት የቀይ ሽብር ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል። በዚህም ኮሎኔል መንግሥቱ በሌሉበት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል።

ስለ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በርካታ መጽሃፎችን የጻፉት እና በለንደን ሳውዝ ባንክ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጋይም ክብረአብ ሁለቱ የቀድሞ መሪዎች መገናኘታቸው አስገራሚ ነው ምናልባትም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አበረታችንት የተከናወነ ነው ይላሉ።

ይለማርያም እና መንግሥቱ እንዴት ሊገናኙ ቻሉ?

አቶ ኃይለማርያም እና ኮሎኔል መንግሥቱ እንዴት ሊገናኙ እንደቻሉ ወይም የተገናኙበትን ምክንያት በሚመለከት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም። ይሁን እንጂ በርካቶች የራሳቸውን ግምት ያስተጋባሉ።

አቶ ጋይም ኃይለማርያም ዚምባብዌ ሳሉ ኮሎኔል መንግሥቱን እንዲጎበኘ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሳይጠየቁ አይቀርም ሲሉ ይጠረጥራሉ። ''ያለ ዓብይ ፍቃድ በምንም አይነት ሁኔታ ኃይለማርያም መንግሥቱን ሊያገኙ አይችሉም'' በማለትም ይከራከራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በቅርቡ በነበረቸው መድረክ ላይ ለኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ ልናደርግ እንችላለን ስለማለታቸውም ተሰምቶ ነበር። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት ''መንግሥቱን ወደ ሃገር እንዲመለስ ቢያደርጉ ብዙም አይደንቀኝም'' ይላሉ አቶ ጋይም።

ይሁን እንጂ በርካቶች ለኮሎኔል መንግሥቱ ይቅርታ ማድረግ ''ፍትህን ማጓደል'' ነው ይላሉ። አቶ ጋይም ጨምረውም ''መንግሥቱ ወንጀለኛ ነው'' ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረወዋል።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሃገር ሸሽተው ከወጡ በኋላ ዚምባብዌ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ መኖሪያቸው ሆና መቆየቷ ይታወቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ