በአሜሪካ ፖሊስ «የምግብ ያለህ!» ያሉ ህፃናትን ህይወት ታደገ

ሕፃናቱ የተገኙበት ስፍራ ከአየር ላይ የተነሳ ምስል Image copyright EPA

በአሜሪካ የኒው ሜክሲኮ ግዛት ፖሊስ 11 በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናትን ከታገቱበት በረሃማ አካባቢ እንደታደጋቸው ገለፀ።

የአካባቢው ፖሊስ እንዳስታወቀው የህፃናቱ ዕድሜ ከ 1 እስከ 15 ድረስ ሲሆን ቡትቶ የለበሱ፣ ባዶ እግራቸውን የነበሩ፤ በአጠቃላይ "የሦስተኛው ዓለም ስደተኞች" ይመስሉ ነበር ሲል ሁኔታቸውን ገልጿል።

በስፍራው ሁለት ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችን ጨምሮ አምስት ትልልቅ ሰዎች ተገኝተዋል።

ፖሊስ አካባቢው ላይ ፍተሻ ያካሄደው "ተርበናል ምግብና ውሃ እንፈልጋለን!" የሚል መልዕክት ከደረሰው በኋላ እንደ ነበር አስታውቋል። ልጆቹ በዚህ ስፍራ እንዴት ሊታገቱ እንደቻሉ የታወቀ ነገር የለም።

አሜሪካ ሩሲያዊቷን በሰላይነት ከሰሰች

"አሜሪካ የስደተኞች ካምፕ እንደትሆን አልፈቅድም"፦ ትራምፕ

ፖሊስ ስፍራውን አነስተኛ የምድር በታች መኖሪያ፣ በላስቲክ የተሸፈነ ፣ መብራትም ሆነ የቧንቧ ውሃ የሌለበት በማለት ነው የገለፀው።

የታኦስ ግዛት ፓሊስ ጄሪ ሆግሬፍ "ለሰላሳ ዓመታት ያህል የፖሊስ አባል ሆኜ አገልግያለሁ፤ እንደዚህ አይነት ነገር አይቼ አላውቅም። የማይታመን ነው" ብለዋል።

"አጥንታቸው እስኪቆጠር ድረስ ከስተዋል። ንፅህናቸውም የተጠበቀ አልነበረም እናም በጣም ተረብሸው ነበር" ሲሉም አክለዋል።

በስፍራው ምንም አይነት የመጠጥ ውሃ ያልተገኘ ሲሆን ምግብ የነበረው ጥቂት ድንችና አንድ ሳጥን ሩዝ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

ሁለቱ የታጠቁት ሰዎች ሲራጅ ዋሃጅ እና ሉካስ ሞርቴን ሲሆኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተጨማሪም ሦስት ሴቶች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ግን ተለቀዋል። አስራ አንዱ ህፃናት በአካባቢው የማህበረሰብ አገልግሎት ባልደረቦች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ