በሶማሌ ክልል በተከሰተው ቀውስ የብዙዎች ህይወት ሲጠፋ አብያተ-ክርስቲያናት መቃጠላቸው ተገለፀ

በሶማሌ ክልል በተነሳው ቀውስ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል Image copyright BBC SOMALI

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ተሰማርቷል ተብሎ መነገሩን ተከትሎ ከቅዳሜ ጀምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ።

የክልሉ መስተዳደር በማዕከላዊው መንግሥት መካከል አለ በተባለው አለመግባባት ሳቢያ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ዋና ከተማዋ ጅግጅጋ በመግባቱ ሁከትና ግርግር እንደተቀሰቀሰ ተገልጿል።

መከላከያ ሠራዊት የክልሉን የፓርላማ አዳራሽ እንዲሁም ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ቅዳሜ ዕለት ተዘግቦ ነበር።

የደቦ ጥቃትና ያስከተለው ስጋት

በድሬዳዋ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም ተባለ

ይህንም ተከትሎ በንግድ ተቋማትና መኖሪያ ቤቶች ላይ ዝርፊያ ሲፈፀም፤ የሶማሌ ብሔር ተወላጅ ባልሆኑ የክልሉ ነዋሪ በሆኑ ግለሰቦች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አብያተ-ክርስቲያናት መቃጠላቸውንና ካህናት እንደተገደሉ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። የዓይን እማኞች በግርግሩ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር አስር ቢያደርሱትም አንዳንዶች ግን ቁጥሩ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ መግባቱን "ህገ-ወጥና ህገ-መንግሥቱን" ያልተከተለ ነው በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል።

የክልሉ ማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊ ኢድሪስ እስማኤል አብዲ ለቢቢሲ ሶማሊኛ እንደተናገሩት "ፌዴራሊዝምን መሰረት ያደረገ ህገ-መንግሥት አለን። በህገ-መንግሥቱም መሰረት የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የሚገባው ከክልሉ አቅም በላይ ሲሆንና በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት ነው። የመከላከያ ሰራዊት ህገ-ወጥ በሆነና ከህገ-መንግሥቱ በሚፃረር መልኩ እኛን ሳንጠይቅ ገብቷል። ለጊዜው መገንጠል አላሰብንም በፌደራል ሥርዓቱም እንተዳደራለን፤ ነገር ግን መገንጠል መጥፎ ሀሳብ አይደለም። ህገ-መንግሥቱም ለዛ ዋስትና ሰጥቶናል" ብለዋል።

በተቃራኒው የክልሉን ርዕሰ-መስተዳደርን በመቃወም በድሬዳዋ ከተማ ስብሰባ ላይ የነበሩ ቡድኖች የመከላከያ ሠራዊቱን መግባት ደግፈውታል።

አቶ አብዲ ስለተናገሩት ጉዳይ እንደማያውቅ ኢህአዴግ ገለፀ

መንግሥት ልዩ ፖሊስን እንዲበትን አምነስቲ ጠየቀ

ከተቃዋሚዎቹም አንዱ ዶ/ር ኑህ ሼክ አብዲ ጋፎው "ፕሬዚዳንቱ ክልሉ ከእሱ አመራር ውጪ ከሆነ ቀውስ እንደሚፈጥር ሲናገር ቆይቷል። ይህንን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥትን ስናስጠነቅቅ ቆይተናል። አሁን ጣልቃ መግባታቸውን እናበረታታለን። የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ክልላችንን ወረውታል የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው። ይህ እኛ የጀመርነው አብዮት ነው። የክልሉ አስተዳደርም ድሬዳዋ ላይ በተደረገው ስብሰባ ደስተኛ ስላልሆኑ ነው ይህንን እየፈፀሙ ያሉት" ብለዋል።

የሃገር መከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የተከሰተው ብጥብጥ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሻገር ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች መዛመቱን አመልክቶ ይህም "በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ሊገታ እና ሊታረም የሚገባው ድርጊት ነው" ብሏል።

መግለጫው አክሎም የሁከቱን መከሰት ተከትሎ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ሁኔታውን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን ለማረጋጋት ጥረት እንዳደረገ ነገር ግን ብጥብጡ በተፈለገው ፍጥነት ሊቆም እንዳልቻል ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በመፈጠሩ ሠራዊቱ ሁከትና ብጥብጡን በዝምታ እንደማይመለከተውና "ሰላም ለማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ" አስጠንቅቋል።

ሁከቱ በተከሰትባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከፍ ያለ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን የት እንዳሉ ሳይታወቅ የቆዩት የክልሉ ርዕሰ-መሰተዳደር አቶ አብዲ ሞሃመድ ኦማር በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው መረጋጋት እንዲፈጠር መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ