መንግሥት ከኦነግ ጋር ለመደራደር ልዑካን ወደ አሥመራ ላከ

ወርቅንሀ ገበየሁ እና ለማ መገርሳ
የምስሉ መግለጫ,

በየውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ እና የኦሮሚያ ፕሬዝደንት ለማ መገርሳ የሚመራው የልዑካን ቡድን ኤርትራ ደርሷል

መቀመጫውን ኤርትራ ባደረገው እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ለመደራደር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ዛሬ ረፋዱ ላይ ወደ ኤርትራ መሄዱን የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዶ/ር ነገሪ እንዳሉት ውይይቱ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይጀመራል። የተቀሩት የልዑካን ቡድኑ አባላት እነማን እንደሆኑ እና ውይይቱ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ማወቅ ግን አለተቻለም።

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ቀደም ሲል ሦስተኛ ወገን በድርድሩ እንዲኖር መጠየቁ የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ኤርትራ በሄዱበት ወቅት ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረው ነበር። በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት መንግሥት ከኦነግ ጋር ያለውን ልዩነት ለምን ማጥባብ እንዳልቻለ ተጠይቀው በቅርቡ ልዑክ እንደሚላክ ገልጸው ነበር።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ነገሪ ይህ ውይይት በስምምነት እንደሚጠናቀቅ እና በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን የደህንነት ስጋትም ይቀርፋል የሚል እምነት አላቸው።