አሜሪካዊቷ የምርቃት ፎቶዋን ለምን ከአዞ ጋር ተነሳች?

ማኬንዚ ከአዞው ጋር

የፎቶው ባለመብት, Makenzie Noland

]በአሜሪካ የኮሌጅ ተማሪዋ የምርቃት ቀንዋ ሁሌም እንዲታወስ ፈልጋለች። ስለዚህ የምርቃት ጋወኗን እስከነ ኮፊያ ለብሳ አዞ ጎን ቆማ ፎቶ ተነስታለች። አዞውም ለፎቶ ተመቻችቶ ታይቷል።

ማኬንዚ ኖላንድ ትባላለች፤ ከቴክሳስ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርስቲ በዱር አራዊትና አሳ ሀብት ሳይንስ አርብ ዕለት ዲግሪዋን ታገኛለች።

ይህች ተመራቂ የስራ ላይ ልምምድ ለማድረግ ወደ ቤይሞንት የእንስሳት ማቆያ ስፍራ በሄደችበት ወቅት 450 የአዞ ዝርያዎችንና ተሳቢ እንሳስትን ተመለከተች።

ከሁሉም እንስሳት ግን ቢግ ቴክስ የተባለው አዞ ልቧን አሸፈተው። ይህ አዞ በ2016 ነው ወደዚህ ማዕከል የመጣው። ማኬንዚና አዞው ቴክስ ለየት ያለ ቅርርብ አዳበሩ።

እርሷ እንደምትለው ሁልጊዜም ልትመግበው ወደሚኖርበት ኩሬ ስትሄድና ስሙን ስትጠራው ይሰማል፤ ለእጅ እንቅስቃሴዋም መልስ ይሰጣል።

የፎቶው ባለመብት, Makenzie Noland

"በየዕለቱ ከእርሱ ጋር ወደ ኩሬው እገባለሁ ከምርጥ ጓደኞቼ መካከል አንዱ ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

የ20 ዓመቷ ወጣት ባደገችበት አካባቢ አዞ በቅርብ አይገኝም አሁን ግን የዕለት ተዕለት ውሎዋ ከእርሱ ጋር ሆኗል።

"ከልጅነቴ ጀምሮ እባብ መያዝ፣ እንስሳትን ማቀፍ፣ ህፃናትን ማዋራትና ማህበረሰቡን ማስተማር እወድ ነበር" በማለት ለዱር እንስሳት ያላት ፍቅር የጀመረበትን ስፍራ ትገልፃለች።

መጀመሪያ ላይ የምረቃ ፎቶዋ በዚህ የበጋ ወቅት የምትሰራውን ስራ እንዲያንፀባርቅ ፈልጋ ነበር።

"እውነታው እነዚህ እንስሳት የምንፈልገው እዛው በሚኖሩበት ኩሬ ወይም ረግረጋማ ስፍራ ብቻ እንዲኖሩ እንጂ ወደ ህይወታችን ልናመጣቸው አንፈልግም" በማለት ስለምትሰራበት ጋተር ማዕከል ታስረዳለች።

" አዞው ቢግ ቴክስ አብሮን እስካለ ድረስ እንስሳትን ማሰልጠን እና ያለውን ሰዋዊ ገፅታ ማሰያት መቻላችን ድንቅ ነው። ድንቅ ፍጥረት ነው ሁሉም ደግሞ ሰወ በላ አይደሉም "

ማኬንዚ ከአዞው ቴክስ ጋር ፎቶዋን ተነስታ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ካጋራች በኋላ ባገኘችው ምላሽ እጅጉን ተገርማለች።

"ይህንን አልጠበኩም ነበር አንድ ሁለት ቆንጆ ፎቶዎችን በኢንስታግራም ገፄ ላይ ማጋራት ብቻ ነበር የፈለኩት፣ አሁን ግን ድንቅ ነው "

ከምረቃ በኋላም ከዱር እንስሳት ጋር መስራቷን መቀጠል ነው የምትፈልገው።

"ከአራዊት አለም ውስጥ ጥልቅ ብዬ መግባት እና ማህበረሰቡን ማስተማር ነው የምፈልገው" ብላለች