የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ አሜሪካ ዳግም የጣለችውን ማዕቀብ አወገዙ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሃኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP PHOTO / HO / IRANIAN PRESIDENCY

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ የአሜሪካን በሃገራቸው ላይ ዳግመኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏን ኮነኑት።

ዛሬ ሥራ ላይ የዋለውን ማዕቀብ "የሥነ-ልቦና ጦርነት" በማለት "በኢራናውያን መካከልም መከፋፈልን ለመፍጠር" ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረትም ማዕቀቡን ተቃውሞ ሕጋዊ የንግድ ሥራ ውስጥ የተሳተፉ ደርጅቶችን ለመከላከል ቃል ገብቷል።

ይህ የትራምፕ ውሳኔ በዚህ ዓመት አሜሪካ ከኢራን የኒውክለር የጋራ ስምምነት ከወጣች በኋላ የተከተለ ነው።

ስምምነቱ በባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን የተደረገ ሲሆን ኢራን የኒውክለር እንቅስቃሴዋን እንድትገድብ በምላሹም የማዕቀብ እረፍት እንድታገኝ የሚያደርግ ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ ስምምነቱ ለአንድ ወገን ያደላ በመሆኑ የኢኮኖሚ ጫናው ዳግም ቢጣል ኢራንን ለአዲስ ስምምነት እንድትንበረከክና ከተንኳሽ ተግባራቷ እንድትታቀብ ያደርጋታል ብለው ያምናሉ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ተነስተው የነበሩትን ማዕቀቦች ዳግመኛ ወደ ተግባር የሚመልስ ሰነድ ፈርመዋል።

ማዕቀቡም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ታላሚ ያደረጉት በኢራን መንግሥት የሚገዙ የአሜሪካ የባንክ ሰነዶች፣ ኢራን በወርቅና በከበሩ ማዕድናት የምታደርጋቸውን ግብይቶች፣ በኢራን የገንዘብ ምንዛሪ የሚደረጉ ግብይቶች ላይና ተያያዥ እንቅስቃሴዎችን ነው።

ሁለተኛው ዙር ማዕቀብ ደግሞ ከኅዳር ወር ጀምሮ ተግባር ላይ ይውላል ተብሏል። በህዳር ወር ሥራ ላይ የሚውለው ማዕቀብ ደግሞ የኢራን የኢነርጂና የባህር ላይ ትራንስፖርት ዘርፍን፣ ከኢራን ማዕከላዊ ባንክ በነዳጅ የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ የውጭ የገንዘብ ተቋማት ላይ ይሆናል።

ሩሃኒ ትራምፕ ዳግመኛ የጣሉትን ማዕቀብ "በዲፕሎማሲ ላይ ጀርባን መስጠት" ሲሉ ገልፀውታል፤ አክለውም "ማዕቀብ ጥሎ እንነጋገር ስሜት አይሰጥም" ብለዋል።

"በዲፕሎማሳዊ ጥረቶችና በመነጋገር ሁሌም እናምናለን፤ ነገር ግን ንግግር መተማመንን ይጠይቃል" በማለት የትራምፕ አስተዳደር የኢራንን የውስጥ ፖለቲካ በአሜሪካ በኅዳር ወር ለሚካሄደው ምርጫ እንደ ቀብድ መያዙን ተችውታል።

የጀርመን የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ የኒውክለር ስምምነቱ ለዓለም ደህንነት "እጅጉን ጠቃሚ" ነው በማለት ገልፀውታል። አክለውም የአውሮፓ ኩባንያዎች ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ማናቸውንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከልከል የተጋረጠ ግድግዳ ሲሉ አስቀምጠውታል።