የአእምሮ መታወክን በሚያስከትሉ ህመሞች ላይ በኢትዮጵያ ጥናት እየተደረገ ነው

አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ በሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, BSIP

ብዙ ገንዘብ ታጠፋለች፤ በሯን ዘግታ ትቀመጣለች ፤ ከሰው በላይ የሆነች ይመስላታል፤ የእንቅልፍ ጊዜዋ በጣም አጭር ነው፤አለባባሷ የተለየ ነው፤ ወሲባዊ ስሜቷ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡

የህመሙ መጠን እየጨመረ በመጣ ቁጥር ራሷን መቆጣጠር ይሳናታል፡፡

ቅሽለቱ ቢያንስ በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ይከሰትባታል።

አስፈላጊው የምክር አገልግሎትና መድኃኒት ሲሰጣት ብቻ መለስ ይልላታል።

ቤተሰብ የተስፋ ጭላንጭል ዐይቶ፤ በፊታቸው ላይ የበራው ደስታ ሳይገለጥ ቅጭም ይላል፡፡

እንደገና ከፍተኛ ድብርት ይወርሳታል፡፡ ራሷን ትጠላለች ፤ ራሷን ታወግዛለች ፤እሷነቷ ያንገሸግሻታል፡፡ እነዚህ ስሜቶቿ ከመጠን በላይ ይሆኑና ራሷን የማጥፋት ፍላጎት ላይ ያደርሳታል ።

ሌት ተቀን እርሷን መጠበቅ የቤተሰብ ሥራ ሆነ፡፡

ስሜቷን የሚያወርድ መድኃኒት ሲሰጣት ወደ ቀደመው ማንነቷ ትመለሳለች። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ሕክምናዋን ተከታተለች፡፡

በጤናዋም ላይ ቀስ በቀስ ለውጥ መታየት ጀመረ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህርና ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ካከሟቸው ሰዎች መካከል የዚችን ወጣት የጤና ጉዳይ እንደ አብነት ያነሳሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ትዳር መሥርታ፣ ልጅ ወልዳ፣ ልጇን እያሳደገች፤ ሕይወቷን በተገቢው መልኩ እየመራች እንደሆነ ለቢቢሲ የገለፁት ፕሮፌሰር መስፍን መልካም አጋጣሚውን ያስታውሱ እንጂ ለባሰ የአእምሮ ህመም ተዳርገው ራሳቸውን ያጠፉ እንዳሉም አይዘነጉም፡፡

ቅሽለት ምንድነው?

ቅሽለት አንዳች የአእምሮ ጤና መጓደል ነው። በሕክምና ስሙ ሀይፖማኒያ (Hypomania) በመባል ይታወቃል።

መገናኛ ብዙኃን በስፋት የሚያወሷቸው የስሜት መዋዠቅ (Bipolar) እና የአስተሳሰብ መዛባት (Schizophrenia)፣ በዚሁ ቅሽለት (Hypomania) በተሰኘው የአእምሮ ሕመም ሥር የሚጠቀሱ ከባድ የአእምሮ ጤና ችግሮች ናቸው።

አንድ ሰው ራሱን ሲያገል፣ ከሰው ጋር ለመቀላቀል ሲፈራ ፣ ትካዜ ሲያበዛ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ሲጠላ፣ ቤት መቀመጥ ሲጀምር፣ ለድብርት እየተጋለጠ መሆኑንና ይህም እያደገ ሲሄድ የአስተሳሰብ መዛባት (Schizophrenia) ወደተባለው የአእምሮ ህመም እየተጠጋ ለመሆኑ አመላካች ነው ።

ለዚህ ሕመም የተጋለጡ ሰዎች ከእውነታ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተዛባ ነው፡፡

ምክንያታዊ ያልሆነ ጥርጣሬንና ሐሳብን ሊያስቡ ይችላሉ፤ በስሜት ህዋሶቻቸው አማካኝነት በገሃዱ ዓለም የሌሉ ስሜቶች ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ ምንም ሰው በሌለበት ሁኔታ የለሆሳስ ድምጽ ሊሰሙ ይችላሉ፤ ዕይታ ውስጥ የሌለን ነገር ይመለከታሉ፡፡

ማኅበራዊ ሕይወታቸው ይቃወሳል፣ ሥራ መሥራት ይሳናቸዋል፡፡ በስሜት ወጀብ ይናጣሉ፡፡

ወጀቡ ቅሽለት (Hypomania) የተሰኘው ሕመም ላይ ይጥላቸዋል ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ።

ሌላኛው የአእምሮ ጤና እክል የስሜት መዋዠቅ ነው፡፡ Bipolar!

ይህም የሁለት ስሜቶች መዛነፍ ውጤት ሲሆን ታማሚው ምክንያታዊ ያልሆነ ደስታ፣ ሐዘንና እንዳንዴም ከባድ ድብታን ያስተናግዳል፡፡

በዚህ ህመም የተጠቁ ሰዎች ከመሬት ተነስተው በሳቅ ሊንከተከቱ ይችላሉ፤ አሊያም ምንም ሰበብ አስባብ በሌለበት በእንባ ይታጠባሉ፡፡

ስሜታቸው ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት ይጎድለዋል።

ይህ ደግሞ ለታማሚም፣ ለአስታማሚም ፣ ለሐኪምም ፈተናው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

እነዚህ የአእምሮ ሕመሞች ከ0.5 እስከ 1 በመቶ ሥርጭት እንዳለው የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ አንደ ቀላል የሚታይ አይደለም ይላሉ።

በመሆኑም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የጤና ችግር ሲያጋጥም ሌሎች የቤተሰቡ አባላት አሊያም የትዳር አጋር እገዛ ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ የጥናቱ መዳረሻ

በቅርቡ ለእነዚህ ከባድ የአእምሮ ሕመሞች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ያለመ ዓለም አቀፍ ሰፊ የጥናት እቅድ በኢትዮጵያ ይፋ ተደርጓል።

ዶክተር ሰለሞን ተፈራ በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም በኢትዮጵያ የጥናቱ አስተባባሪ ናቸው፡፡

ጥናቱ ከባድ የአእምሮ ህመም የሚባሉትን የአስተሳሰብ መዛባት (Schizophrenia)፣ እንዲሁም የስሜት መዋዠቅ (Bi-polar) ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ይላሉ፡፡

ዓላማውም የእነዚህን የጤና ችግሮች የዘር መሠረታቸውን ፣ አጋላጭ ዘሮችን(Genes) ፣ የሚከሰትባቸውን ምክንያቶችንና የሕክምና ዘዴዎችን በመለየት ሕክምናውን ማፈላለግ ነው፡፡

በዚህ ዓለም አቀፋዊ ጥናት ከአፍሪካ አህጉር ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ደቡብ አፍሪካ የጥናቱ አካል ሆነዋል፡፡

"ከፍተኛ የሆነ የዘር ስብጥር ያላቸው በመሆኑ፣ ልዩ ልዩ የዘር መዋቅሮችን ለማግኘት ያስችላል፤ በባህሪው ነባር ሕዝብ በመሆኑ ለጥናቱ ጠቃሚ መረጃ ሊገኝበት ይችላል" ይላሉ የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን።

ካሁን ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን የተወሰዱት ናሙናዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ይህም የአእምሮ ጤና ችግሮቹን በስፋት ያሳዩ እንዳልነበሩ ይገልጻሉ፡፡

"የአእምሮ ጤና እክሎቹ ሁሉንም የሰው ዘር የሚያጠቁ በመሆናቸው በአገራት መካካል ያለው ሥርጭትም ተመሳሳይነት አለው" የሚሉት ዶክተር ሰለሞን በኢትዮጵያ ከመቶ ሰዎች አንዱ ለእነዚህ የአእምሮ ህመሞች ይጋለጣል ይላሉ፡፡

ሰማኒያ በመቶ በዘር የሚተላላፍ በመሆኑ በአገራት መካከል ያለው ሥርጭት ያን ያህል ልዩነት እንደሌለው ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም ዓለምአቀፋዊ የሆነ መፍትሄ ለመፈለግ ኤዥያ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ሰሜን አሜሪካም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከእነዚህ ክፍለ ዓለማት የተሰባሰቡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በዓለም ላይ የሰው ዘርን ይወክላሉ የተባሉ የዘረ መል ናሙናዎች ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እና ኤም አይ ቲ በጋራ በሚመሩት ቤተ-ሙከራ ጥናት ይደረግባቸዋል፡፡

ይህም ከአራት እስከ አምስት ዓመታት ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

እኔ ከሞትኩ ሰርዶ ይብቀል

እንደዚህ ያሉ ጥናቶችን ለማካሄድ የገንዘብ አቅም የሚጠይቁ በመሆናቸው በስፋትና በጥልቀት ለማጥናት የማይደፈር መሆኑ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡

ይህ ጥናት በአንድ በጎ ፈቃደኛ አሜሪካዊ ቢሊየነር ቴድ ሰታንሊ የኑዛዜ ገንዘብ የሚደገፍ ነው፡፡ ለጥናትና ምርምሩ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ሐብታቸውን ነው ተናዘው ያለፉት።

ለዚህ በጎ ተግባር ያነሳሳቸው ደግሞ ልጃቸው የስሜት መዋዠቅ (Bi-polar) ህመም ተጠቂ መሆኑ ነበር። እርሱን ለማዳን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ልጃቸውን መታደግ አልቻሉም፡፡

በልጃቸው ላይ የደረሰው በሌላ ላይ አይድረስ ሲሉ "ስታንሊ ሴንተር"ን መሥርተው በአእምሮ ጤና ችግሮች ላይ አብዝተው ይሠሩ ነበር፡፡

እርሳቸውም በቅርቡ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ዘለቄታ ያለው መድኃኒት ለእኔ ልጅ ባይደርስ እንኳን ለሌሎች ይድረስ ሲሉ ጠቅላላ ሐብታቸውን ለዚህ በጎ ተግባር እንዲውል ተናዘዙ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራው ይህ ጥናት የሚደገፈው ቢሊየነሩ ቴድ ስታንሊ በተናዘዙት ገንዘብ መሆኑን ዶክተር ሰለሞን ጨምረው ተናግረዋል፡፡