የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ፍርድ ቤት ቀረቡ

የኤምዲሲ ጥምረት አመራር የሆኑት ቴንዳይ ቤቲ ፍርድ ቤት ቀርበዋል Image copyright AFP

የዚምባብዌ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ቴንዳይ ቢቲ በዛምቢያ ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ብጥብጥን በማነሳሳት በእጅ ካቴና ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በዚህ ሳምንት ረቡዕ እለት ዛምቢያ የፖለቲከኛውን ጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ አድርጋዋለች።

አቃቤ ህግ ቴንዳይ ቢቲን የፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋን አሸናፊነት በመቃወም "ህገ-ወጥ" የተቃውሞ ሰልፍ በማቀጣጠል ከሷቸዋል።

ምርጫውን አንቀበልም ባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችና በፀጥታ ኃይሎችና በተፈጠረ ግጭት የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል።

"የምንመለሰው ያፈረሰን የምርጫ ቦርድ እራሱ ከፈረሰ ብቻ ነው'' ልደቱ አያሌው

በኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ላይ ጭማሪ ሊደረግ ነው

በሕንድ የሚማሩ ኢትዮጵያዊያን ''ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል'' አሉ

የተቃዋሚው ደጋፊዎች አመራሩን ኔልሰን ቻሚሳን የምርጫው ውጤት ተሰርቆባቸዋል እንጂ እሳቸው አሸናፊ ናቸው ብለዋል።

ከሮበርት ሙጋቤ የ37 ዓመታት አገዛዝ በኋላ የተደረገው ይህ ምርጫ አገሪቷን ወደ ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫ ይመራታል ተብሎ ታምኖ የነበረ ቢሆንም፤ የኤምዲሲ ጥምረት የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጭቆና፣ እንግልት አድርሰውብናል በማለት ይወነጅሏቸዋል።

ኤመርሰን ምናንጋግዋ ስልጣን ከያዙ በኋላ በከፍተኛ ባለስልጣን ደረጃ ሲያዙ ቴንዳይ ቢቲ የመጀመሪያው ናቸው።

በእጅ ካቴና ታስረው የቀረቡት ቴንዳይ ቢቲ በመዲናዋ ሀራሬ በፖሊስ ታጅበው ቀርበዋል።

አቃቤ ህግ በሀሰት ኔልሰን ቻሚሳን የምርጫው አሸናፊ በማድረግ የፓርቲው ደጋፊዎች ንብረት እንዲያወድሙ አበረታተዋል በማለት ወንጅሏቸዋል።

ቴንዳይ ቢቲ በአምስት ሺ ዶላር ዋስ የወጡ ሲሆን ፓስፖርታቸውን እንዲያስረክቡ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

ከወጡ በኋላም "በትግላችን እንቀጥላለን" በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው በሳቸው ጣልቃ ገብነት ቴንዳይ እንደተፈቱ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

"በዚህ ታሪካዊ በሆነ ወቅት ለዚምባብዌ ከአንድነት፣ ሰላምና ንግግር በላይ የሚጠቅማት ምንም ነገር የለም" ብለዋል።

ነገር ግን ምናጋግዋ እንዳሉት ቴንዳይ ቢቲ የተወነጀሉበት ክስ ከፍተኛነት ምክንያት የፍርድ ሂደቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እንዳለው ቴንዳይ ቢቲ የፖለቲካ ጥገኝነት ዛምቢያ ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋላቸው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ስደተኞችንም ሆነ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በኃይል ወደ ሀገራቸው መመለስ የአለም አቀፍ የስደተኞችን ህግ መጣስ ነው" በማለት መግለጫው አትቷል።

የቴንዳይ ቢቲ ጠበቃ ጂልበርት ፊሪ በበኩላቸው የዛምቢያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በፍርድ ውድቅ እስካልተደረገ ድረስ ከሀገር እንዳይባረሩ የሚል ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ተናግረዋል።

ነገር ግን የዛምቢያ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱን ወረቀት ባለመቀበልና በመጣስ ለዚምባብዌ ባለስልጣናት አስተላልፈው ሰጥተዋቸዋል ብለዋል።

የዛምቢያ መንግሥት ቴንዳይ ቢቲን ከኃገር ያስወጧቸው ለበቀል እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ባለፈው አመት ቴንዳይ ቢቲ ወደ ዛምቢያ መጥተው የተቃዋሚው ፖርቲ መሪ ሀካይዴ ሀቺሌማ በሀገር ክህደት ተወንጅለው በነበረበት ወቅት ድጋፋቸውንም ሰጥተው ነበር።

የሰላ ትችታቸውንም በመሪው ላይ ከማቅረብ በተጨማሪ ከሮበርት ሙጋቤ ጋር አወዳድረዋቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ