ኢትዮጵያ-በምስራቅ ሐረርጌ 37 ሰዎች ሲገደሉ 44 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው

መዩ ሙሉቄ

ትናንት ምስራቅ ሃረርጌ ውስጥ በምትገኘው ሙዩ ሙሉቄ በምትባል ወረዳ ውስጥ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ፈጽሞታል በተባለው ጥቃት የ37 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና 44 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው የኮሙኑኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ትዝታ አባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል 36 የሚሆኑት ሰዎች በሙዩ ሙሉቄ ወረዳ ጤና ጣቢያ ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ እና የተቀሩት ደግሞ ወደ ጋራ ሙለታ ሆስፒታል እንደተወሰዱ የወረዳው የጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱላሂ አህመድ ካዎ ነግረውናል።

የወረዳዋ ነዋሪ የሆኑት እና በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው በሙዩ ሙሉቄ ጤና ጣቢያ ውስጥ የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙት አቶ ሞሃመድ ሲራጅ ''በቤት ውስጥ ተቀምጠን ባለንበት ወቅት የሶማሌ ልዩ ፖሊሶች በር ገንጠለው ገቡብን። ባለቤቴን፣ ልጄንና የሁለት ዓመት የጎረቤት ልጅ አጠገቤ ገደሉ'' ሲሉ የደረሰባቸውን ጉዳት ተናግረዋል።

''ልቤ ላይ መቱኝ፣ ቀኝ ጆሮዬን ቆርጠው የሞትኩ መስሏቸው ትተውኝ ሄዱ'' ይላሉ አቶ ሞሃመድ።

እሳቸው በጤና ጣቢያው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ፤ የልጃቸውና የባለቤታቸው አስክሬን መኖሪያ ቤታቸው እንዳለ ጨምረው ተናግረዋል።

ሌላው በጤና ጣቢያ ህክምና እየተደረገላቸው የሚገኙት የወረዳዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዲ አብዱላሂ ''በትልልቅ የጦር መሳሪያዎች ተኩስ ከፈቱብን። እኔም እጄን ተመትቻለሁ'' ይላሉ።

የልዩ ፖሊስ አባላቱ መኖሪያ ቤቶች እንዳጋዩ እና ንብረት ዘርፈው እንደሄዱ ጨምረው ተናግረዋል።

ሙዩ ሙሉቄን ጨምሮ ቡርቃ እና ሮጌ በተባሉ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ ተኩስ መከፈቱን ነግረውናል።

''ሴቶች፣ ዓይነ ስውር አዛውንቶች እና ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በጥቃቱ ተገድለዋል'' በማለት የደረሰውን ጉዳት የሙዬ ሙሉቄ ወረዳ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ትዝታ ነግረውናል።

አክለውም ''ወረዳዎቹን የሚያገናኙ መንገዶች በልዩ ሃይሉ በመዘጋታችው እርዳታ መስጠት አልተቻለም፣ አስከሬን ያልተሰበሰበባቸው ቦታዎች ሁሉ አሉ'' ብለዋል።

እንደ ወ/ሮ ትዝታ ከሆነ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ጥቃቱ ሲፈጸም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረ ቢሆንም ጥቃቱን ግን ማስቆም አለመቻሉን ተናግረዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከት የሶማሌ ክልል መንግሥትን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።