በአዳማና በቴፒ በደረሰ ግጭት የሰው ህይወት አልፏል

የአዳማና የቴፒ ካርታ

ትናንት ከኢትዮ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በአዳማ ከተማ ተጠልለው በሚገኙና በአካባቢው ኗሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ 18 የሚሆኑ ደግሞ መጎዳታቸውን የአዳማ ከተማ ፖሊስ ዋና ሳጅን ወርቅነሽ ገልሜቻ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

"በዚህ መካከል ድንጋይ በመወርወር የተጎዱ ሰዎች አሉ።አራት ቤቶች ተቃጥለዋል። "ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 17 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ያጋጠመ ሲሆን፤ እነዚህም ሆስፒታል ገብተው ህክምና አግኝተው የወጡ ሲሆን አንድ ሰው ግን ህይወቱ ማለፉንም ተናግረዋል።

በአዳማ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ትምህርት እያጠና የሚገኘው ዶ/ር ዲዳ ባቱ ደግሞ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከ30 በላይ እንደሆነ ሲገልፅ ዋና ሳጅን ወርቅነሽ በበኩላቸው የግጭቱ መንስኤ እየተጣራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በቴፒ ከተማ ደግሞ በተመሳሳይ ግጭት ዛሬ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ሌላ አንድ ሰው መጎዳቱን የከተማዋ ፍትህና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ግጭቱ ከትናንት የጀመረ ሲሆን ምንም እንኳ ትናንትና በመኖሪያ ቤቶች ላይ እና በመንግስት ተቋማት ላይ ጉዳት ቢደርስም የሰው ህይወት እንዳልጠፋ ነገር ግን ዛሬ ነገሩ ተባብሶ አንድ ሰው መሞቱን አቶ ተስፋየ አለሙ ይናገራሉ።ሌላ አንድ ሰውም ሆስፒታል መግባቱንና ብዙዎች ላይም ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ ስለታማ መሳሪያዎችን የያዙ እንደነበርና ይህም ነገሩን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ማዋልን አዳጋች እንዳደረገው አስረድተዋል።

አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት የተፈጠረው ችግር ብሄርን ምክንያት ያደረገ ሲሆን መንስኤው በወጣቶች መካከል የተፈጠረ ግጭት ነው።

ግጭቱን ተከትሎ በከተማዋ በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተወሰነ መልኩ ነገሮች መርገባቸውንና ከተማዋን ለማረጋጋትም የመከላከያ ሃይል መግባቱን የፀጥታ ሃላፊው ገልፀዋል።

"አሁን የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው። ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተረጋግታለች ባይባልም የመከላከያ መግባትን ተከትሎ ነገሮች ረግበዋል።"ብለዋል አቶ ተስፋዬ።