ካለሁበት 44፡ "በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መኖሩን ሳረጋግጥ ነው ወደ ሃገሬ የምመለሰው’’

የመን ኤደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስሜ ካሚል አህመድ አደም ይባላል።

ተወልጄ ያደግኩት በምስራቅ ሀረርጌ ጨርጨር ወረዳ ነው አግብቼ አንድ ልጅ አፍርቻለሁ።

በወቅቱ ባጋጠመኝ ችግር ከመሞት መሰንበት በማለት የትውልድ ስፍሪያዬን ለቅቄ ከሀገር ወጣሁ።

በአሁኑ ወቅትም በየመን ሀገር ኤደን በሚትባል ከተማ ነው የምኖረው።

ስደትን ሀ ብየ የጀመርኩትም በሀገር ወስጥ እያለሁ ወደ ኢሉባቦር ዞን በመሸሽ ነበር።

እዚያም ሄጄ የንግድ ስራ ጀመረኩ እንዲሁም ወደ 12 ሺህ የሚጠጉ የባህር ዛፍ ችግኞችን ተክየ ነበር።

ይሁን እንጂ በማላውቀው መንገድ ብዙም ሳልቆይ ንብረቴን በሙሉ በመውስድ ችግኞቼንም በማውደም እኔን እስር ቤት ወርውረው ያሰቃዩኝ ጀመር።

እኔም በደረሰብኝ መከራና ችግር የተነሳ መደበኛ ስራዬን መስራት ባለመቻሌ ተቸገርኩኝ፤ በዚህም የተነሳ ቤተሰቦችን ትቼ ከሀገር ለመውጣት ተገደድኩኝ።

ከአምስት አመት በፊትም ከኢሉባቦር በመነሳት በጂቡቲ በኩል የመን ኤደን ገባሁ።

ሌላ አማራጭ ከማጣት የተነሳ እንጂ የመን የሚሸሽበት ሀገር አይደለችም።

የየመን ዜጎችን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ድጋፍ አያደርጉልንም፤ ፍትህን ነስተውናል።

በዚህ ሀገር የስደተኛ መብት የሚጠበቅላቸው ለሱማሊያ ስደተኞች ብቻ ነው። ሶማሌዎች ወደዚህ ሀገር መምጣት ከጀመሩ 40 አመት በላይ ስላስቆጠሩ በሀገሪቷ የበለጠ እውቅናን አግኝተዋል።

ስለዚህ እንደ ምግብ ፤ የጤና እንክብካቤ፤ ወደ ሶሰተኛ ሀገር መላክም ሆነ በየመን ሀገር ውስጥ መኖር እኩል ተጠቃሚ አይደለንም። ከሀገሩ ህዝብ ጋር ተመሳስሎ መስራትና መኖር ለሱማሌዎች የበለጠ ይቀላል።

የኢትዮጵያ ስደተኞች ኑሮ ፈታኝና ብዙ ጥሰት ስለሚደርስብን በዚህ ሀገር እየተፈፀመብን ያለውን ነገር አለም እንዲያውቅልን እንፈልጋለን።

የፎቶው ባለመብት, Kamil Ahmed Adam

ከሶስት አመታት በፊት በሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት የአረብ ኤምሬት የመንን በጥምረት በአየር በደበደቡበት ወቅት በዚህ ከተማ ውስጥ የቀረነው እኛና አሞራዎች ብቻ ነበርን።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ትራንስፖርት በመላክ ከጦርነቱ እንደያስወጣን ቢንጠይቅም የሚደርስልን አካል አላገኘንም።

በወቅቱ በተደረገው ጦርነትም የየመን ዜጎችን ጨምሮ ብዙ ህዝብ ሞቷል። እኔም ለትንሽ ነው የተረፍኩት።

የመን ብዙ ባህላዊ የምግብ አይነት አላት። በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያለው እኔም የምወደው ኩፍዚ የሚባል ባህላዊ ምግብ አለ።

ከስንዴ ዱቄት በተዘጋጀ ቂጣ፣ በአሳ ስጋ ከሚሰራ ማባያ ጋር ይበላል፤ጣፋጭም ነው።

የፎቶው ባለመብት, MOHAMMED HUWAIS

ከሀገሬም ብዙ ነገሮች ይናፍቁኛል ለምሳሌ ተራራዎቹ እና ወንዞቹ ሁሌም አልረሳቸውም።

የድድሳ እና ደባና ወንዞች እንዲሁም የአባስና ተራራን ሁሌ በሀሳቤ ሽው ይሉብኛል።

አሁን በምኖርበት የየመን ኤደን ከተማ ውስጥ አንድም ደስ የሚያሰኝ ቦታ የለም። የሀገሪቱ መሰረት ልማት አውታሮች በሙሉ በጦርነቱ ወድመዋል።

በዚያ ላይ የሽንት ቤት ፍሳሾች በየመንገዱ ስለሚፈሱ የከተማውን ሽታ ለውጦታል። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በከተማው አንድም የሚስብ ቦታ የለም።

ስልጣን ቢኖረኝ በዚህ ሀገር ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት የመጀመሪያ ስራዬ ይሆን ነበር።

በተጨማሪም እንደኛ ያሉት ጥቁር ሰዎች መብት እንዲከበር እሰራ ነበር።

በዚህ ሀገር ካጋጠሙኝ ችግሮች መካከል ከስድስት አመታት በፊት የተለያዩ የ12 ሀገራት መንግስታት የመንን በጋራ በደበደቡበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪው ወቅት ነበር።

ብዙ ሰዎችም ከአጠገባችን ስለሞቱ ያን ጊዜ ፈታኝ ነበር።

በሀገራችን እየታየ ያለው ለውጥ እንደ አንድ ሰው ደስ ይለኛል። ነገር ግን አሁንም ገና የሚቀሩ ነገርች እንዳሉ ይሰማኛል። ብዙ ቦታዎች ላይ አሁንም ሰላም የለም።

ይህንን እየሰማሁ እንዴት ልመለስ?

ተገቢው መፍትሄ ለህዝባች ከተሰጠና ዘላቂ ሰላም መረጋገጡን ባወኩኝ ግን በደስታ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ።

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረው