ደቡብ አፍሪካዊው ዘረኝነትን አስመልክቶ ባሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ከስራው ተባረረ

አዳም ካትዛቭሎስ የተባለው ግለሰብ በውሃ ዳርቻ

የፎቶው ባለመብት, Adam Catzavelos

የምስሉ መግለጫ,

የደቡብ አፍሪካ የባህል ሚንስተር ግለሰቡ የተጠቀመው ቋንቋ በህብረተሰቡ ቦታ የለውም ብለዋል

ደቡብ አፍሪካዊው ግለሰብ ዘረኝነትን የሚያነፀባርቅ ንግግሮችን የያዘ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ ይሰራበት ከነበረው የቤተሰቦቹ የንግድ ስራ ተሰናብቷል።

ይህ አዳም ካተዛቭሎስ የተባለ ግለሰብ በውሃ ዳርቻ አካባቢ ሆኖ የቀረፀው ተንቀሳቃሽ ፊልም "ጥቁር ህዝቦች ባይኖሩ ኖሮ ገነት ምድር ላይ ነበረች" የሚል ዘረኛ መልዕክትንም አስተላልፏል።

እንደዚህ ያለ ደቡብ አፍሪካውያንን የሚያሳንስ የንቀት ንግግር በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት ነጮች ይጠቀሙበት የነበረ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 1994 የነጮች የበላይነት ካበቃለት በኋላ የዘረኝነት ንግግሮች በአገሪቱ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህም ምክንያት በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ዘረኛ ንግግር ያደረገች ሴት ለእስር ተዳርጋለች።

አዳም ካተዛቬሎስም ያሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት በመዘዋወሩ በተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።

ከመነጋገሪያነቱም አልፎ የትዊተር ተጠቃሚዎች ቅመማ ቅመሞችንና ምግብ በማምረት የሚታወቀውን የቤተሰቡን ድርጅት "ማንም ሰው እንዳይጠቀም" የሚል ዘመቻ ጀምረዋል።

ድርጊቱ ደቡብ አፍሪካውያንን አሳዝኗል፤አስቆጥቷል።

አንዳንዶቹ ግን ከቁብም አልቆጠሩት፤ ምክንያቱ ደግሞ የነጮች የበላይነት እንደቀጠለ ነው ብለው በማመናቸው ነው።

ይህ ደግሞ እንደ ተራና የተለመደ ነገር እንዲቆጠር እያደረገው ነው ተብሏል።

መንግስት እንዲህ ዓይነት ዘረኛ ንግግሮችን ለመግታት የሚያስችል እቅድ እያወጣ ይሁን እንጂ መልዕክቱ በሚገባ ሁሉም ጋር የደረሰ አይመስልም ።

"በዚህ ግለሰብ ላይ የሚጥለውን ቅጣት ማየት እንፈልጋለን። በአገሪቱ ያሉ ጥቁር ህዝቦች ትዕግስታቸውና ይቅር ባይነታቸው ከልክ እያለፈ ነው" ሲሉ የተደመጡም ነበሩ።

የግለሰቡ ወንድም ኒክ ካተዛቬሎስ በበኩሉ "በሰማነው ነገር ቤተሰቡ ሁሉ ተሸማቋል፤ በማንኛውም መንገድ ዘረኛ አስተሳሰብን ማስወገድ ያስፈልጋል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በዚህም ምክንያት ወዲያውኑ ከቤተሰቦቹ የንግድ ስራ እንዲባረር ሆኗል፤ ያለው ድርሻም በቅርቡ ይነጠቃል ብለዋል።

የድርጅቱን ሰራተኞች ደህንነት ለመጠበቅም ሲባልም ለጊዜው ድርጅቱ መዘጋቱን አስታውቋል።

የአገሪቱ የባህል ሚንስትር ናቲ ምቴትዋ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነት የጥላቻ ንግግሮች የሚወገዙ ናቸው።

"ሁላችንም ይህንን ለመታግል አብረን ልንሰራ ይገባል፤ ድርጊቱን የሚፈፅሙትን ሰዎችም ወደ ህግ ማቅረብ አለብን ብለዋል።

የግለሰቡን ጉዳይ ወደ ህግ ያመራልም ተብሏል።