በሮም 'ፋውንቴን' ስር እርቃናቸውን ሆነው ሲዝናኑ የነበሩ ግለሰቦች በጣሊያን ፖሊስ እየታደኑ ነው

የሁለቱ የውጭ አገር ቱሪስቶች በፏውንቴኑ' ስር ሲቦርቁ

የፎቶው ባለመብት, @RomaFaSchifo/Twitter

በጣሊያን ሃውልት ፏፏቴ ስር እርቃናቸውን ሲቦርቁ የነበሩ ሁለት እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጎብኝዎች በጣሊያን ፖሊስ እየተፈለጉ ነው።

የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማቴዎ ሳልቪኒ "ቅሌታሞች" ብለዋቸዋል።

ሁለቱ ጎብኝዎች በሮም ፒያሳ ቬንዚያ በተባለ ፋውንቴን ስር እየተዝናኑ ሳለ አንደኛው የለበሰውን የውስጥ ሱሪ በማውለቅ ለፎቶግራፍ ራሱን በማዘጋጀቱ ነው።

ፎቶግራፉ ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን "እፍረተ ቢስ" ሲሉም አራክሰዋቸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ "ጣሊያን የእነርሱ መታጠቢያ ቤት አይደለችም" ሲሉ ድርጊታቸውን ኮንነዋል።

በሮም በሚታወቅ 'ብሎግ' የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስሉ ጎብኝዎቹ ከ'ፏውንቴኑ' ስር ሃፍረተ ስጋቸውን እየነካኩ ሲታጠቡ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

በወቅቱ አንድ በመንገድ የሚያልፍ ሰው ፎቶግራፍ ያነሳቸው ሲሆን ከ'ፋውንቴኑ' እንዲወጡ የሞከሩም ነበሩ።

ሌሎች በአካባቢው ሲተላለፉ የነበሩ መንገደኞች ግን ራሳቸውን በአግራሞት እየነቀነቁ አልፈዋቸዋል።

የአገሪቱ ፖሊስ ድርጊቱን አሳፋሪና ህገ ወጥ እንደሆነ ገልጾ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እያደረገ ነው።

ሁለቱ ጎብኝዎች የውጭ አገር ዜጎችና እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሆናቸውን ደርሸበታለሁ ብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩም "እነዚህ እፍረተ ቢሶች ይገኙ እንጂ፤ እንዴት እንደማስተምራቸው አሳያቸዋለሁ!" ሲሉ ዛቻቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

'ፋውንቴኑ' ለጣሊያን የመጀመሪያ ንጉስ መታሰቢያ የተሰራና የተሰው ወታደሮች የሚታሰቡበት ሐውልት ስር የሚገኝ ነው።