ኡጋንዳዊው ሙዚቀኛና ተቃዋሚ የፓርላማ አባል በሃገር ክህደት ክስ ተመሰረተበት

ቦቢ ዋይን ለደጋፊዎቹ ሳለምታ ሲሰጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኡጋንዳዊው ተቃዋሚ የፓርላማ አባልና ታዋቂው ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን የሃገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በነጻ ካሰናበተው በኋላ በድጋሚ በሃገር ክህደት ክስ ቀርቦበት በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተወስኗል።

ቦቢ ዋይን ትክክለኛ ስሙ ሮበርት ክያጉላኒ ሲሆን፤ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ካሰናበተው በኋላ ወዲያው ነው በድጋሚ በቁጥጥር ስር የዋለው።

ጠበቃዎቹ በቁጥጥር ስር በዋለበት ሰዓት ድብደባ ደርሶበታል ቢሉም፤ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒም ሆነ የመከላከያ ሃይላቸው ውንጀላውን አልተቀበሉትም። ቦቢ ዋይንን ጨምሮ ሌሎች 30 ሰዎችም ከባለፈው ሳምንት የማሟያ ምርጫ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የእነዚህ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋል በሃገሪቱ ውጥረትን አንግሷል። ፖሊስም ከፍተኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ከቤት እየወሰደ ነው።

የኡጋንዳው ታዋቂ ጋዜጣ '' ኒው ቪዥን'' በፊት ገጹ ይዞት እንደወጣው ከሆነ ቦቢ ዋይን በወታደራዊ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት የመዳከም ምልክት ታይቶበት ነበር። በወቅቱ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ነበር ክስ የቀረበበት።

ጠበቃው ደንበኛቸው አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ያስፈልጋቸውል ማለታቸውንም ጋዜጣው ገልጿል።

የሃገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም ብሎ በነጻ ካሰናበተው በኋላ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ከባለቤቱ ጋር በፖሊስ መኪና ተጭነው ተወስደዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የቦቢ ዋይን ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ ባደገረጉበት ወቅት የመከላከያ ሃይሎች እርምጃ ወስደውባቸዋል። በወቅቱ አንድ ጋዜጠኛ ድበዳባ ሲደርስበት የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተሰራጨ በኋላ የኡጋንዳ ሰራዊት ይቅርታጠይቋል።