ቶዮታ ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ሊያሰማራ ነው

የኡበር መኪናዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው የጃፓን የመኪና አምራች ኩባንያ ቶዮታ ''ኡበር'' የተባለው የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ጋር አብሮ ለመስራት 500 ሚሊዮን ዶላር ሊመድብ ነው።

በየመንገዱ የሚሰማሩት መኪናዎች ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ተጠቃሚዎች ስልኮቻቸው ላይ በሚጭኗቸው የኡበር መተግበሪያ በኩል ጥሪ ሲያቀርቡ ተሽከርካሪዎቹ ያሉበት ድረስ መጥተው አገልግሎቱን ይሰጧቸዋል።

ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱትን መኪናዎች በብዛት አምርቶ በቅርብ ዓመታት ወደ አገልግሎት ለማስገባት እንዳሰበ ቶዮታ ገልጿል።

ተሽከርካሪዎቹ ተጠቃሚዎቹ ያሉበት ቦታ ድረስ መጥተው በማንሳት ወደሚፈልጉት ቦታ ማድረስ እንዲችሉ የሚያደርጋችው የፈጠራ ውጤት በቶዮታ ባለሙያዎች ተሰርቶ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።

የሙከራ ጊዜው በታሰበለት ጊዜ የሚጠናቀቅ ከሆነም ተሽከርካሪዎቹ በ2021 አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ቶዮታ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የቶዮታ መኪና አምራች ኩባንያ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሺጄኪ ቶሞያማ እንዳሉት በድርጅታቸውና ''በኡበር'' መካከል የተደረሰው ስምምነት ለደንበኞቻቸው ደህንነቱ የተጠበቀና ገደብ የሌለበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ለማገዝ ነው።

ከዚህ በፊት ግን አሜሪካ ውስጥ ''በኡበር'' አማይነት ያለአሽከርካሪ የሚሰራ መኪና ለሙከራ ተሰማርቶ ባደረሰው አደጋ የአንድ ግለሰብ ህይወት መጥፋቱ የሚታወስ ነው።

ከቶዮታ ጋር የተደረሰው ስምምነት እንደዚህ አይነት አደጋዎችን ለማስቀረት እንደሆነ ተገልጿል።