በሊቢያ በተፈጠረ ግጭት ከአራት መቶ በላይ እስረኞች አመለጡ

ብዙ ሊቢያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሊቢያዋ መዲና ትሪፖሊ በሚሊሺያ ቡድኖች መካከከል በተፈጠረ ግጭት ከአራት መቶ በላይ እስረኞች አምልጠዋል።

"እስረኞቹ በሩን በኃይል ከፍተው" አይን ዛራ ተብሎ ከሚጠራው እስር ቤት መውጣት እንደቻሉ የአካባቢው ፖሊስ ገልጿል።

የእስር ቤቱ ጠባቂዎችም የነበረውን ረብሻ በመፍራት እስረኞቹን ከማስመለጥ መቆጣጠር አልቻሉም ነበር።

በተለያዩ ሚሊሺያ ቡድኖች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው የሊቢያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አስተላልፏል።

በተፎካካሪ ሚሊሺያ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ይህ ቀውስ የወንዶች እስር ቤት አጠገብ ነው።

ከትሪፖሊ በደቡብ ምስራቅ ክፍል የሚገኘው አይን ዛራ እስር ቤት የሚገኙ አብዛኛው እስረኞች የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ደጋፊ እንደሆኑ ተገልጿል።

ለእስር የተዳረጉትም በአውሮፓውያኑ 2011 ተፈጥሮ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ግድያን ፈፅመዋል በሚል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በዛኑ ዕለት በትሪፖሊ የተወነጨፈ ሮኬት የተፈናቃዮች መጠለያን መትቶ ሁለት ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ብዙዎችም ቆስለዋል።

የሊቢያ የጤና ሚኒስትር እንደገለፁት አርባ ሰባት የሚሆኑ ሰዎች በሚሊሺያዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ህይወታቸውን እንዳጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም ቆስለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው መንግሥት በመዲናዋ ተቀማጭነቱን ቢያደርግም፤ የተለያዩ የሚሊሺያ ቡድኖች መላ ሀገሪቷን ተቆጣጥረዋታል።