በናይጄሪያ አዲሱ የማዋለጃ ቦርሳ የእናቶችን ህይወት እየታደገ ነው

ፔጁ ጄዬኦባ በናይጄሪያ ለጤናማና ንጹህ ወሊድ ጠቃሚ ምርቶችን የያዙ ግማሽ ሚሊዮን ህይወት አድን የማዋለጃ ቦርሳዎችን አሰራጭታለች።
የምስሉ መግለጫ,

ፔጁ ጄዬኦባ በናይጄሪያ ለጤናማና ንጹህ ወሊድ ጠቃሚ ምርቶችን የያዙ ግማሽ ሚሊዮን ህይወት አድን የማዋለጃ ቦርሳዎችን አሰራጭታለች።

"እንዳንዴ የእኛ ሥራ የማያስፈልግበት አንድ ቀን እንዲመጣ ከልብ እመኛለሁ" ትላለች የናይጄሪያው ብራውን በተን ፋውንዴሽን መስራች አዴፔጁ ጄዬኦባ።

ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር አዴፔጁ በቁልምጫ ስሟ 'ፔጁ' ለናይጄሪያ የልምድ አዋላጆች የማዋለድ ስልጠና ለመስጠት ስትል ከፍተኛ ክፍያ የምታገኝበትን የሕግ ሥራ የተወችው።

ከባክቴሪያ የጸዱ ወሳኝ የህክምና ቁሶችን የያዘ ቦርሳም አዘጋጅታ በናይጄሪያ ገጠራማ አካባቢዎች በአነስተኛ ዋጋ እየተሸጠ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል።

ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ ሥራቸውን እንዳትለቅ ሊያሳምኗት ቢሞክሩም በወሊድ ምክንያት የቅርብ ጓደኛዋን በማጣቷ ሌላ አማራጭ አልታያትም።

"ጓደኞዬ የተማረች ነበረች፤ እናም የገንዘብ ችግር የሌለበት ሰው በወሊድ ምክንያት የሚሞት ከሆነ 'አገልግሎቱ ባልተሟሉባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ምን ሊፈጠር ይችላል?' ብዬ እንዳስብ አስገደደኝ።"

"በእጅጉ ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ በድጋሚ ሌላ ሰው ማጣት አልፈለግኩም ነበር፤ ለአንዱ ህይወትን የመስጠት ሂደት የሌላኛውን ሰው ሕይወት ማሳጣት አለበት ብዬ አላስም።"

የምስሉ መግለጫ,

ህጻናት በናይጄሪያ በሚሸጠው ቦርሳ ውስጥ በሚገኘው አነስተኛ ምንጣፍ ላይ ይለወዳሉ።

የመፍትሄ እርምጃ

ከሃኪም ወንድሟ ጋር በመሆን በገጠር የሚኖሩ ሴቶች እንዴት ባለ ሁኔታ አንደሚወልዱ በውል ለመረዳት ከሌጎስ በስተሰሜን ወደ ሚገኝ ስፍራ አቀናች።

ያገኘችው ነገርም በእጅጉ የሚረብሽ ነበር።

"ሴቶች በባዶ መሬት ላይ ሲወልዱ፣ ነርሶችም ጨቅላዎቹ እንዳይታፈኑ ፈሳሹን በአፋቸው ሲስቡ ተመለከትን" ትላለች።

"አዋላጆች አትብት በዛጉ ምላጮችና ብርጭቆ ስባሪ ስለሚቆርጡ ጨቅላዎች በመንጋጋ ቆልፍ ሲያዙ ብዙዎችም ሲሞቱ አየን።"

"እጆችን መታጠብና ጓንት ማጥለቅን የመሰሉ መሰረታዊ ነገሮች እንኳ እዚህ ትልልቅ ጉዳዮች ናቸው።"

በናይጄሪያ በየቀኑ 118 እርግዝናዎች በሞት ይቋጫሉ፤ ሀገሪቱ ከወሊድ ጋር የተያያዘ የእናቶች ሞት በከፍተኛ ቁጥር ከሚመዘገብባቸው ሃገራት አንዷ ናት።

ሂደቱ በጣም አሳሳቢ ነው የምትለው ፔጁ፤ ብዙዎቹ ወላዶች ወሊድን ከመንፈሳዊ ገፅታው አንጻር ስለሚመለከቱት ንፅህናቸውን ከጠበቁ የህክምና መገልገያዎች ይልቅ ባህላዊ መድሃኒቶችና ጸሎት ጥቅም ላይ ወደሚውሉባቸው የባህል ሃኪሞች ዘንድ መሄድን ይመርጣሉ።

የምስሉ መግለጫ,

የፔጁ ቦርሳዎች ዋነኛ አላማቸው ለባክቴሪያ የመጋለጥ ዕድልን መቀነስ ነው።

አስፈላጊውን ማሟላት

ፔጁ የልምድ አዋላጆችን በዘመናዊ የማዋለጃ ዘዴዎች ለማሰልጠን ብራውን በተን የተሰኘውን ድርጅትን መስረተች።

በወቅቱ ይህ መንገድ ለማዋለጃ ቦርሳው ሁነኛ የስርጭት ሰንሰለት እንደሚያበጅላት ግን ብዙም አልተረዳችውም ነበር።

እንዴት ተጀመረ

"በሌጎስ የምንገዛቸው ነገሮች በሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል በጣም ውድ እንደሆኑ ተገነዘብኩኝ። ለምሳሌ ጓንት በሦስት እጥፍ ሊወደድ ይችላል።"

አምራቾች በርካሽ ዋጋ ለዚያውም ሌጎስ ከሚሸጥበትም ዋጋ በታች እልፍ ሲልም በገጠራማ አካባቢዎች ከሚሸጥበትም ባነሰ ዋጋ እንዲሸጡላቸው በደንብ ተከራክረው ለመነሻ የሚሆናቸውን 30 እሽጎችን ነበር የገዙት።

"እንዲህም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች አሁንም ቢሆን ቦርሳውን የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ነገሩን" ትላለች ፔጁ።

"ነገር ግን ለማዋለጃ ቦርሳው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማጠራቀም የዘጠኝ ወር ጊዜ አላቸው፤ በእያንዳንዱ የቅድመ ወሊድ ምርመራ ጊዜ መዋጮ ቢያስቀምጡ በመውለጃቸው ጊዜ ክፍያው ይጠናቀቃል።"

የምስሉ መግለጫ,

እናቶች ቦርሳው የሚያወጣውን አራት ዶላር በዘጠኝ ወራት የእርግዝና ጊዜያቸው መክፈል ይችላሉ።

ቦርሳው ከባክቴሪያ ማጽጃ ጀምሮ ንጹህ ጓንት፣ የእትብቱ መቁረጫ ምላጭ፣ በምጥ ጊዜ የሚነጠፍ አነስተኛ ምንጣፍና ከወሊድ በኋላ ከፍተኛ ደም መፍሰስን የሚቀንሱ መድሃኒቶችንና ሌሎች 13 አይነት መገልገያዎችን ይዟል።

የአንዱ ቦርሳ ዋጋ 4 ዶላር ገደማ የሚያወጣ ሲሆን በውስጡ ከያዛቸው መገልገያዎች መካከል አብዛኞቹ እዚያው ናይጄሪያ ውስጥ የሚመረቱ ናቸው።

ባለፉት አራት ዓመታት ብራውን በተን ፋውንዴሽን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የማዋለጃ ቦርሳዎችን አሰራጭቷል።

ፋውንዴሽኑ እንደሚለው ስልጠናውና የቦርሳው አቅርቦት በጥምረት በተሰጡባቸው አካባቢዎች ከወሊድ በኋላ በሚከሰት ከፍተኛ የደም መፈስሰ የሚሞቱት ወላዶች ቁጥር በአንድ አራተኛ ቀንሷል።

"ለጤናማ ወሊድ የሚያገለግሉት እነዚህ ቦርሳዎች በወሊድ ወቅት እናቲቱንም ሆነ ጨቅላውን ከቁስል መመርቀዝ (ኢንፌክሽን) መከላከሉ ጥሩ ሃሳብ ነው ምክንያቱም የቁስል መመርቀዝ ወላዶቹን ለሞት ከሚዳርጉ መንስዔዎች አንዱ ነው" ብለዋል በሌጎስ ዩኒቨርስቲ የማህጸንና የጽንስ ህክምና መምህር የሆኑት ቦሴዴ አፎላቢ።

"ንጹህ ጓንት፣ ንጹህ የማዋለጃ ቦታ እና እንግዴ ልጁና እትብቱ የሚለያዩበት ንጹህ መቁረጫ ካለ በባክቴሪያ የመጠቃት ዕድሉን ይቀንሳል።"

የምስሉ መግለጫ,

ፔጁ ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ስትገናኝ የሚያሳየውን ፎቶ በጠረጴዛዋ ላይ በክብር አስቀምጣዋለች።

ኦባማ ወይስ የስልክ ማጭበርበር?

አንድ ቀን ፔጁ ቢሮ ስትገባ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከነበሩበት ኋይት ሃውስ ከሚገኝ አንድ ሰው የስልክ መልዕክት ይደርሳታል።

እቤት ሄዳ ስለዚሁ መልዕክት ለባሏ ከነገረችው በኋላም ቢሆን የሆነ ሰው እየቀለደባቸው ሊሆን አንደሚችል ነበር የተስማሙት።

"ለማንም የምስጢር ቁጥርሽንም ሆነ የባንክ አካውንት ቁጥርሽን እንዳትሰጪ" አላት።

ሆኖም በእርግጥም መልዕክቱ የመጣው ከኋይት ሃውስ ነበር። ከእያንዳንዱ አህጉር የፈጠራ ሰዎችን ሲጋበዙ ፔጁ ከአፍሪካ እንድትሄድ ተመርጣ ነበር።

"ወደ ኋይት ሃውስ ስገባ እስታውሳለሁ ህልም ነበር የመሰለኝ" ትላለች። "ስለአፍሪካ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት እና ስለ ጤና ክብካቤ አወራን፣ በሥራዬም ትልቅ ለውጥ እንዳስመዘገብ አድርጎኛል።"

ይህ የቢቢሲ ተከታታይ ዝግጅት የሚቀርበው በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የእናቶችንና የሕፃናትን ህይወት እየታደገ ያለው ቦርሳ