የሰኞ ነሐሴ 28፤ 2010 ዓ.ም አጫጭር ዜናዎች

ታማኝ በየነ

የፎቶው ባለመብት, Tamagne Beyene

  • ዓለም አቀፍ በረራዎችን አስተጓጉለዋል፤ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ሥራ ማቆም አድማም አስተባብረዋል የተባሉ 9 አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መታሰራቸውን ፌደራል ፖሊስን በመጥቀስ ፋና ዘግቧል።
  • የቀድሞ የአሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጁነዲን ሳዶ በስደት ይኖሩበት ከነበረው አሜሪካ ዛሬ ኢትዮጵያ ገቡ። በተመሳሳይ ቅዳሜ ዕለት ኢትዮጵያ የገባው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በየነ ዛሬ በባህርዳር ስታዲየም ለበርካቶች ንግግር አድርጓል።
  • በሊቢያ ትሪፖሊ አቅራቢያ ከሚገኝ እስር ቤት ከአራት መቶ የሚበልጡ እስረኞች ማምለጣቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
  • እስረኞቹ ያመለጡት በከተማዋ በታጣቂ ቡድኖች መካከል ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ ሲሆን ለነፍሳቸው የፈሩት የእስር ቤቱ ጠባቂዎችም ሸሽተዋል።
  • በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሠላሳ የዲሞክራሲ አቀንቃኞች ታሰሩ። ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት ታኅሳስ ወር ላይ በአገሪቱ በሚደረገው ምርጫ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበውን የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት በመቃወም ነው። የአገሪቱ ፖሊስ ከሰልፈኞቹ የተወሰኑትን እንደለቀቀ አስታውቋል።
  • በደቡብ አፍሪካ በሥራ ገበታችን መገለል ደረሰብን ያሉ ስድስት ሺህ ነጭ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ። ባለሙያዎቹ ፔትሮኬሚካልስ የተሰኘ ኩባንያ ሠራተኞች ሲሆኑ የሥራ ማቆም አድማቸውም ለሦስት ሳምንታት እንደሚቆይ ተገልጿል።
  • በሪዮ ዲጄኔሮ የሚገኘው የብራዚል ሙዚየም በእሳት ተቃጠለ። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አጋጣሚዉን የአገሪቱን የሁለት መቶ ዓመት ጥናትና እውቀት ያጠፋ አሳዛኝ ክስተት ብለውታል። ቀድሞ ብሔራዊ ቤተመንግሥት የነበረው ሙዚየሙ በአሜሪካ የተገኘውን የጥንታዊ ሰው ቅሪት ጨምሮ ሃያ ሚሊዮን ቅርሶች ነበሩበት ተብሏል።
  • ማይናማር ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞች ላይ የሰባት ዓመት እስር ፍርድ አስተላለፈች። ጋዜጠኞቹ የተፈረደባቸው የአገሪቱን የምሥጢራዊነት ሕግ ተላልፈዋል በሚል ነው። በማይናማር የአሜሪካ አምባሳደር የማይናማር መንግሥት እርምጃ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ሲገልፁ የአውሮፓ ኅብረት ጋዜጠኞቹ በፍጥነት እንዲለቀቁ ጠይቋል።
  • ስዋዚላንድ በቤጂንግ እየተካሄደ ያለውን የቻይና አፍሪካ ስብሰባ የማትካፈል ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ሆነች። በቅርቡ ምስዋቲ ብላ ስሟን የቀየረችው ስዋዚላንድ በቻይና አፍሪካ ስብሰባ ያልተገኘቸው አጋርነቷ የቻይና ባላንጣ ከሆነችው ታይዋን ጋር በመሆኑ ነው።